የዴንማርክ ግብ ጠባቂ ፊት ላይ ጨረር ከተለቀቀ በኋላ እንግሊዝ ላይ ክስ ተመሠረተ

የዴንማርክ ግብ ጠባቂ ካስፐር ሽማይክል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዴንማርክ ግብ ጠባቂ ካስፐር ሽማይክል

በትናንት ምሽቱ የእንግሊዝ እና ዴንማርክ የአውሮፓ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ በተከሰቱ ክስተቶች እንግሊዝ ላይ ክስ ተመሠረተ።

በተጨማሪ ሰዓት የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ፍጹም ቅጣት ምት አግኝቶ ፍጹም ቅጣት ምቱን ሊመታ ሲል የዴንማርኩ ግብ ጠባቂ ካስፐር ሽማይክል ፊት ላይ የጨረር ብርሃን መታየቱን ተከትሎ እንግሊዝ ላይ ክስ ተመስርቷል።

እንግሊዝ በተጨማሪ ሰዓት ያገኘችውን ፍጹም ቅጣት ምት የፊት መስመር ተጫዋቹ ሃሪ ኬን ሊመታ ሲል በግብ ጠባቂው ፊት ላይ የጨረር ብርሃን የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።

በርካታ የእግር ኳስ ወዳጆች ጨረሩ የግብ ጠባቂው ዓይኖችን ኢላማ ማድረጉን በመጥቀስ ግብ ጠባቂው በጨረሩ ብርሃን ማየት ተስኖት ፍጹም ቅጣቱ በቀላሉ እንዲቆጠርበት ታስቦ ነው በማለት የእንግሊዝ ደጋፊዎች ላይ የሰላ ትችት እየሰነዘሩ ይገኛሉ።

ሽማይክል የተመታውን ፍጹም ቅጣት ምት ቢመልሰውም ኳሷ ግብ ጠባቂውን ገጭታ ከሃሪ ኬን እግር ስር ገብታ ወደ ጎል ተቀይራለች። ይህ ጎል እንግሊዝ የፊታችን እሁድ ለሚደረገው የፍጻሜ ጨዋታ እንድታልፍ ረድቷል።

የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካላት የጨረሩ ምንጭ ከየት እንደሆነ የማጣራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዴንማርክ ብሔራዊ መዝሙር እየተዘመረ ሳለ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች መረበሻቸው እና ርችት መተኮሳቸው ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዴንማርክ ብሔራዊ መዝሙር እየተዘመረ ሳለ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች መረበሻቸው እና ርችት መተኮሳቸው ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የዴንማርክ ብሔራዊ መዝሙር እየተዘመረ ሳለ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች መረበሻቸው እና ርችት መተኮሳቸው ተገልጿል።

ይህ የእንግሊዝ ደጋፊዎች ተግባር በዩናትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንሰትር ቦሪስ ጆንሰን ቃል አቀባይ ተተችቷል።

"ደጋፊዎች ብሔራዊ ቡድኖችን እንዲያጥላሉ እንፈልግም" ያሉ ሲሆን ቃል አቀባዩ ጨምረውም፤ "ደጋፊዎች ድጋፍ እና ክብር እንዲያሳዩ ነው የምንፈልገው" ብለዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የዴንማርክ ብሔራዊ ቡድን በጉዳዩ ላይ ይፋዊ ቅሬታ ማቅረብ የሚፈልጉ እንደሆነ ተጠይቀው 'ጉዳዩን ወደ ሌላ ደረጃ መውሰድ እንፈልግም' ማለታቸው ተዘግቧል።

የአውሮፓ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል የሆነው ዩኤፋ ጉዳዩ በቁጥጥር እና ሥነ ምግባር አካል የሚታይ ይሆናል ብሏል።