ከአንድ ሳምንት በፊት የተያዙት የሚዲያ ባለሙያዎች ያሉበት አይታወቅም ተባለ

ከአንድ ሳምንት በፊት ከሁለት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ተይዘው የነበሩት ባለሙያዎች የት እንደሚገኙ እንደማይታወቅ ጠበቃቸው ተናገሩ።
የሚዲያ ባለሙያዎቹ ከታሰሩ ከአንድ ሳምንት በላይ ቢያልፋቸውም እስካሁን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና ያሉበትን ቦታ ቤተሰቦቻቸው ማወቅ እንዳልቻሉ ጠበቃቸው ታደለ ገብረመድህን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ኢትዮ ፎረም በተባለ የዩቲዩብ ቻናል ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞች እና የአውሎ ሚዲያ ማዕከል ባልደረቦች በፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው መዘገቡ ይታወሳል።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የሆነው ሲፒጄ የባለሙያዎቹን እስር በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፤ መንግሥት ያሰራቸውን ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ባለሙያዎች በአስቸኳይ እንዲለቅ እና በሙያው የተሰማሩ ግለሰቦች ላይ ያሚያደርሰውን ጫና እንዲያቆም ጠይቋል።
ሲፒጄ ሰኔ 23/2013 ዓ. ም. እኩለ ቀን ላይ ፖሊስ አዲስ አበባ ወደሚገኘውን አውሎ ሚዲያ ማዕከል በኃይል መግባቱን እና 12 የማዕከሉን ሠራተኞች ማሰሩን ጉዳዩን በቅርብ ከሚያውቁ ሰምቻለሁ ብሏል።
በተመሳሳይ ኢትዮ ፎረም በተባለ ዩቲዩብ ቻናል አማካይነት ዜና እና ትንታኔ ያቀርቡ የነበሩት አበበ ባዩ እና ያየሰው ሽመልስ የተባሉ ባለሙያዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል።
ጠበቃቸው አቶ ታደለ፤ የሚዲያ ባለሙያዎቹ የተያዙት በፌደራል ፖሊስ መሆኑን እና በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅት በተለምዶ ሜክሲኮ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርምራ ማዕከል መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
"እስከ አርብ (ሰኔ 25/2013 ዓ. ም.) ድረስ ቤተሰብ ሲጠይቃቸው እና ምግብ ሲያደርስ ነበር። ከዛ በኋላ ግን 'ተለቀዋል እዚህ የሉም' ተብለዋል። ቤተሰብ ሊያገኛቸው አልቻለም። ፍርድ ቤትም እስካሁን አልቀረቡም" በማለት ተናግረዋል።
የሚዲያ ባለሙያዎቹ ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ ከመደረጉም በላይ የተያዙበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንዳልተነገራቸው አቶ ታደለ ያስረዳሉ።
"የባለሙያዎቹን እስር በተመለከተ ፖሊስ በአንድ መገናኛ ብዙኃን ሲጠየቅ ባለሙያዎቹ የታሰሩት ከአሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት ስላላቸው ነው የሚል ምላሽ እንደሰጠ አንብቤያለሁ። ከዛ ውጪ ግን ለእኛ በግልጽ አልተነገረንም" ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ የፌደራል ፖሊስ አስተያየትን ለማካተት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
ጠበቃው፤ ባለሙያዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከሚዲያ ሥራቸው ጋር በሚገናኝ ነው ብለው ያምናሉ።
"ቤተሰብ በጣም ተጨንቆ ወደ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሄደው አቤቱታ አቅርበው ነበር። ሰኞ እና ማክሰኞ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብለን እየጠበቅን ነበር ግን ሳይቀርቡ ቀርተዋል" ብለዋል።
በአገሪቷ ሕጎች ላይ የዘፈቀደ እስር ሊኖር እንደማይገባ ተመልክቷል የሚሉት ጠበቃው፤ ደንበኞቻቸው በተያዙ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ነበረባቸው በማለት የአገሪቷ ሕግ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል ይላሉ።












