በሁለት የሚዲያ ተቋማት የሚሰሩ 15 ባለሙያዎች መታሰራቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Gerasimov174
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት በሁለት የሚዲያ ተቋማት የሚሰሩ 15 የሚዲያ ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የሆነው ሲፒጄ ገለጸ።
ሲፒጄ የሚዲያ ባለሙያዎቹን እስር በተመለከተ ትናንት ባወጣው መግለጫ መንግሥት በቅርቡ ያሰራቸውን ጋዜጠኞችን እና የሚዲያ ባለሙያዎችን በአስቸኳይ እንዲለቅ እና በሙያው የተሰማሩ ባለሙያዎች ላይ ያሚያደርሰውን ጫና እንዲያቆም ጠይቋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ማህበር በበኩሉ የአውሎ ሚድያ እንዲሁም የኢትዮ ፎረም ባልደረቦች የሆኑ የሚድያ ባለሙያዎች በፀጥታ አካላት ቁጥጥር ስር እንደዋሉ መረጃ ደርሶኛል ካለ በኋላ ማህበሩ ባለሙያዎቹ ስለተያዙበት አካሄድ እና አሁን ስላሉበት ሁኔታ ከሚመለከታቸው አካላት መረጃ ለማግኘት ጥረት እያደረኩ እገኛለሁ ብሏል።
ሲፒጄ ሰኔ 23 እኩለ ቀን ላይ ፖሊስ በአዲስ አበባ በሚገኘውን አውሎ ሚዲያ ማዕከል በኃይል መግባቱን እና 12 የማዕከሉን ሰራተኞች ሰለማሰሩ ጉዳዩን በቅርብ ከሚያውቁ ሰምቻለሁ ብሏል።
ከቀናት በፊት በቁጥጥር ሥር የዋሉት የሚዲያ ባለሙያዎቹ እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን እና ለመታሰራቸው ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዳልተነገራቸው ሲፒጄ ጨምሮ አስነብቧል።
በተመሳሳይ ኢትዮ ፎረም በተባለ ዩቲዩብ ቻናል አማካይነት ዜና እና ትንታኔ ያቀርቡ የነበሩ አበበ ባዩ እና ያየሰው ሽመልስ የተባሉ ባለሙያዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል።
"የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት የኢትዮ ፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ማዕከል በአስቸኳይ መልቀቅ አለበት" ሲሉ የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ አንጄላ ኩይንታል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ማህበር "በጋዜጠኞቹ መያዝ ዙርያ በቂ መረጃ ማግኘት ባንችልም የሚመለከተው የመንግሥት አካል በህግ ከለላ ስር የሚገኙ እነዚህ ባለሙያዎች በተቻለ መጠን በፍጥነት ፍርድ ቤት የመቅረብ፣ የህግ ድጋፍ የማግኘት እንዲሁም የመጎብኘት መብታቸው እንዲጠበቅላቸው እንዲያደርግ ጥሪውን ያቀርባል" ብሏል።












