ግብጽ ስዊዝ ቦይን ዘገቶ የነበረውን መርከብ ለመልቀቅ ተስማማች

ቦይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከመርከቡ ባለቤትና መድህን ሰጪ ጋር ከስምምነት ከደረሰች በኋላ ግብጽ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የስዊዝ ቦይ እንቅስቃሴ ለመስተጓጎሉ ምክንያት የነበረችውን መርከብ ለመልቀቅ ፍቃዷ ሆኗል።

ግብጽ ለድርድር በመያዣነት ያቆያቻትና 'ኤቨር ጊቭን' የሚል ስያሜ ያላት መርከቧ ነገ [ረብዕ] ወራትን ከቆየችበት ቦዩ ለቃ እንደምትወጣ ከሁለቱም ወገን ተሰምቷል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረሰው ስምምነት ጭብጥ ባይታወቅም ግብጽ ግን 550 ሚሊዮን ዶላር ካሳ መጠየቋ ታውቋል።

400 ሜትር የምትረዝመው 'ኤቨር ጊቭን' በከፍተኛ ንፍስ ከተመታች በኋላ ነበር አቅጣጫዋን ስታ በመቀርቀር ቦዩን የዘጋችው።

እናም መርከቧን ከተቀረቀረችበት በማላቀቅ ቦዩን ወደ መደበኛ ስራው ለመመለስ ስድስት ቀናትን የፈጀ ሲሆን በሂደቱ አንድ ሰው ሞቷል።

193 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሜዲትራንያንን ባህር ከቀይ ባህር ጋር የሚያገናኘው እና በእስያ እና በአውሮፓ መካከል አጭሩን የባህር ላይ መንገድ የሆነው ሲዊዝ ቦይ በተዘጋበት በመቶዎች የሚቆጠሩ መርከቦች ለመቆም በመገደዳቸው የዓለም ንግድ አስተጎጉሎት ነበር።

የ'ኤቨር ጊቭን' ሶስተኛ ወገን መድህን ሰጪ የሆነውና 'ዩኬ ክለብ' የተባለው ኢንሹራንስ ባለቤት ሾይ ኪሰን ከሱዊዝ ቦይ ባለስልጣን ጋር በመነጋገር ጉዳዩን እልባት ለመስጠት "መደበኛ መፍትሄ" ላይ መደረሱን አስታውቋል ፡፡

መርከቡን ለመልቀቅ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም አንስተዋል።

የቦዩ አስተዳደር ስምምነቱ ረብዕ ይደረጋል ያለ ሲሆን በተመሳሳይ ቀን መርከቡ ሊወጣ እንደሚችል አስታውቋል።

የትኛውም ወገን በ'ኤቨር ጊቭን' የተፈጠረውን መጉላላላትና ኪሳራ ለመተካት የሚቀርበውን የካሳ ክፍያ መጠን ይፋ ባያደርጉም የቦዩ አስተዳደር ሊቀመንበር ኦሳማ ራቢ የስምምነቱ አካል የሆነ ተጎታች ጀልባ ግብጽ እንደምታገኝ ተናግረዋል።

የቦዩ አስተዳደር ቀደም ብሎ ከ900 ሚሊዮን ዶላር ባላይ ካሳ ጠይቆ እንደነበር ተሰምቷል።