በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ የሚሰማራው የውጭ ኩባንያዎች ጥምረት ኃላፊ ሾመ

አንዋር ሱሳ

የፎቶው ባለመብት, GPE

በቅርቡ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ጨረታ አሸንፎ ከመንግሥት ጋር ውል የተፈራረመውና ስድስት ኩባንያዎች የተጣመሩበት ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ (ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ)፤ አንዋር ሱሳ የተባሉ ግለሰብን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አድርጎ ሾመ።

ኃላፊው ሳፋሪኮም፣ ሲዲሲ ግሩፕ፣ ቮዳኮም፣ ሱሚቶሞ እና ዲኤፍሲ የተባሉት በዓለም ዙሪያ በቴሌኮም ዘርፍ የካበተ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች በጋራ 850 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ ያደረጉበትና በኢትዮጵያ በመቋቋም ላይ የሚገኘውን የቴሌኮም ኩባንያን ይመራሉ።

አንዋር ተጠሪነታቸው ለኩባንያው ቦርድና መሠረቱን ኬንያ ላደረገው ሳፋሪኮም እንደሚሆን ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ (ጂፒኢ) ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

የተሾሙት ኃላፊ ማን ናቸው?

ከሰኔ 24/2013 ዓ. ም. ጀምሮ ለአዲሱ የቴሌኮም ኩባንያ በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት የተሰየሙት አንዋር ሱሳ ግሪካዊ ሲሆኑ ለቴሌኮሙ ዘርፍ አመራር አዲስ አይደሉም።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ2017 ጀምሮ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የቮዳኮም ኩባንያ ዳይሬክተርና የቮዳካሽ [የሞባይል ገንዘብ ሥርዓት] ሊቀመንበር ሆነው ሠርተዋል።

በዚህ የአመራርነት ዘመናቸው ከደቡብ አፍሪካ ውጪ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ቮዳኮም ትልቁ ኩባንያ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርገዋል ይላል የጂፒኢ መግለጫ።

እንደ መግለጫው ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ አገልግሎት ለሚሰጠው ጥምረት በኃላፊነት የተሾሙት አንዋር በዲሞክራቲክ ኮንጎ ቆይታቸው ቮዳኮም በአገሪቱ እንደ አውሮፓውያኑ 2020 ላይ 500 ሚሊዮን ዶላር የአገልግሎት ገቢ እንዲያገኝ ያስቻለ አመራር ሰጥተዋል።

ከዚህ ኃላፊነታቸው በፊት በኡጋንዳ እና በቻድ የኤርቴል የቴሌኮም ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የሠሩ ሲሆን፤ ኤምቲኤንን ጨምሮ በተለያዩ ኩባንያዎች በተለያዩ የአመራር ደረጃዎች ሠርተዋል።

በግሪክ አሜሪካን ኮሌጅ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁት ኃላፊው፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ካናዳ ከሚገኘው ኮንኮርዲያ ዩኒቨርሲቲ ማግኘታቸውን መግለጫው ያትታል።

ኃላፊው ምን ይሠራሉ?

በኢትዮጵያ እየተቋቋመ ያለውን የመጀመሪያውን የውጭ የቴሌኮም ኩባንያ የሚመሩት አንዋር፤ በግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ የተወጠኑ ግቦችን የማሳካት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

ግቦቹም በኢትዮጵያ ማኅበራዊና የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ አወንታዊ ተጽዕኖ መፍጠርና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሕይወት ማሻሻል እንደሆነ በመግለጫው ተመላክቷል።

በሌላ በኩል ኃላፊው በኢትዮጵያ በርካታ ሰዎችን በቴሌኮም ተጠቃሚ ለማድረግ ጥራት ያለውና ተመጣጣኝ የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል ዕቅድ ያዘጋጃሉ።

በኢትዮጵያ ከ125 ዓመታት በላይ በኢትዮ-ቴሌኮም ብቻ ተይዞ የነበረውን ዘርፍ ለመቀላቀል ጨረታ ያሸነፈው ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ ከዓመት በታች በሆነ ጊዜ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይጠበቃል።

ተቋሙ የሚጠበቅበትን 850 ሚሊየን ዶላር ለመንግሥት ገቢ ማድረጉን የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን ያስታወቀ ሲሆን፤ ተጨማሪ የቴሌኮም ኩባንያ ወደ ሥራ ለማስገባት ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል።