አሜሪካ ሚያሚ ውስጥ ከተደረመሰው የመኖሪያ ህንጻ ህይወት ለማዳን ጥረት እተደረገ ነው

በከፊል የፈረሰው ህንጻ

የፎቶው ባለመብት, CBS

አሜሪካ ውስጥ ከማያሚ በስተሰሜን አቅጣጫ በፈረሰ ባለ12 ፎቅ የመኖሪያ ሕንፃ ፍርስራሽ ውስጥ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት የነፍስ አድን ሠራተኞች ጥረት እያደረጉ ነው።

ባለሥልጣናት ቢያንስ በአደጋው የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ 99 ሰዎች ደረሱበት አልታወቅም።

ቤተሰቦች የዘመዶቻቸውን ዜናን በጉጉት በሚጠባበቁበት ወቅት የነፍስ አድን ቡድኖች ሌት ተቀን በመሥራት ከፍርስራሾቹ ውስጥ የሰዎችን ድምጽ ለመስማት እየሞከሩ ነው።

አርባ ዓመታትን ያስቆጠረው ህንፃ ሐሙስ ማለዳ የፈረሰበት ምክንያት እስከ አሁን ድረስ ግልጽ አይደለም።

እስካካሁን ቢያንስ 102 ሰዎች የተገኙ ሲሆን ህንፃው ሲፈርስ ምን ያህል ሰዎች በውስጡ እንደነበሩ አይታወቅም ተብሏል። በሕይወት የተረፉ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ከፍርስራሾች ውስጥ ወጥተዋል።

ሌሊቱ ገፍቶም በመቶዎች የሚቆጠሩ የነፍስ አድን ሠራተኞች በህይወት የተረፉ ሰዎችን ከፍርስራሾች ውስጥ ለማግኘት ካሜራዎችንና የሰለጠኑ ውሾችን እየተጠቀሙ ነው። ተጎጂዎችን ለመድረስ ሠራተኞቹ ከህንጻው በታች ባለው የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ገብተዋል።

የማያሚ የፖሊስ ዳይሬክተር ፍሬዲ ራሚሬዝ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት "የእሳት እና የነፍስ አድን ሠራተኞች ከፍለጋ ቡድኖቻቸው እና ከውሾቻቸው ጋር ፍርስራሾቹ ውስጥ ናቸው" ብለዋል።

"በፍለጋ እና በነፍስ ማዳን ላይ ናቸው። እዚያው ይቆያሉ። ሌሊቱን ሙሉ በሥራ ያሳልፋሉ። አያቆሙም።"

ባለሥልጣናት ተጨማሪ ፍርስራሾች በላያቸው ላይ ሊወድቁ ስለሚችሉ የነፍስ አድን ጥረቶቹ አደገኛ ናቸው ብለዋል።

"ሂደቱ ዘገምተኛ እና ስልታዊ ነው። የመዋቅሩን መንካት በጀመርን ቁጥር ፍርስራሽ በላያችን ላይ ይወርዳል" ሲሉ የማያሚ የእሳት አደጋ ኃላፊ የሆኑት ሬይ ጃዳላህ ገልጸዋል።

በአካባቢው ያለው የማያቋርጥ ዝናብ እና አውሎ ነፋስ ከባዱን የፍለጋ እና የነፍስ ማዳን ሥራ ውስብስብ አድርጎታል።

ባለስልጣናት ቤተሰቦቻቸው ፍርስራሹ ስር የሚገኙ ሰዎችን ዘመዶች ዘረ መል በመሰብሰብ በህይወት ባይገኙ እንኳን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችላቸውን ሥራ ጀምረዋል።

ቤተሰቦች ከተደረመሰው ህንፃ ጥቂት ርቀው በአንድ ማዕከል በመሰባሰብ መረጃ እየጠበቁ ሲሆን በጣም የከፋውን እንዳይመጣም ሰግተዋል።

ኒኮላስ ፈርናንዴዝ ለዘመዶቹ ያደረገው ጥሪ መልስ ያላገኘ መሆኑን ተናግሯል።

ለሲቢኤስ እንደተናገረው "ሳስበው ህይወታቸው ያለፈ ይመስለኛል። ክፉ አሳቢ መሆን ባልፈልግም በተደጋጋሚ ያደረግነው የስልክ ጥሪ ምላሽ አላገኘም" ብሏል።

ጄኒ ዩርጌልዝ ከእንቅልፏ ስትነቃ ነበር ወላጆቿ የሚኖሩበት ህንጻ የመደርመሱን ዜና የሰማችው። ብትደውልላቸውም የሁለቱም ስልክ በቀጥታ ወደ ድምጽ መልዕክት ይመራታል።

"ተስፋ አለኝ። ምን እየሆነ እንዳለ ለማወቅ በጣም ጓጉቻለሁ" ሰትል ለአካባቢው የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግራለች።

ህንጻው ሲደረመስ የዓይን እማኞች ነጎድጓድ ከሚመስል ድምጽ ከሰሙ በኋላ ከፍተኛ የአቧራ ደመና ማየታቸውን ገልጸዋል። አንደኛው የዓይን እማኝ ትዕይንቱን በኒው ዮርክ መንትያ ህንጻዎች ላይ መስከረም 11/2001 ከደረሰው ጥቃት ጋር አመሳስሎታል።

ህንጻው ለምን ተደረመሰ?

እስካሁን ምንም የታወቀ ነገር የለም። የነፍስ አድን ተዕኮው ከተጠናቀቀ በኋላ ሙሉ ምርመራ እንደሚጀመር ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ህንፃው እአአ በ1980 መሠራቱን ተከለትሎ የ40 ዓመት ዕድሜ አለው። የህንጻው ባለቤቶች ደኅንነቱ እንደተጠበቀ የሚያረጋግጥ "ሰርተፊኬት ለማግኘት" ጥረት እያደረጉ የነበረ ሲሆን ባለሥልጣናት ጥገና ይፈልጋል ሲሉ ተናግረው ነበር።

የማያሚ ከንቲባ ዳንኤልላ ሌቪን ለጋዜጠኞች እንደገለጹት "ግልጽ መዋቅራዊ ችግሮች ስለነበሩት ህንጻው ፈርሷል" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ህንጻውን ያጠኑ ባለሙያዎች ያልተረጋጋና ከ1990ዎቹ ጀምሮ እየሰመጠ ነበር ብለዋል።

በፍሎሪዳ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርስቲ ተደረገ የአንድ ተመራማሪ ጥናት እንዳመለከተው በእርጥበታማ መሬት ላይ ተገነባው ህንጻ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በዓመት በሁለት ሚሊሜትር እየሰመጠ ነበር። ይህም በህንጻው መዋቅር ላይ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል ብሏል።

የፍሎሪዳ አገረ ገዢ ሮን ዴሳንቲስ ከፍተኛ በሚባል የህንፃ ውድመት ጉዳት ለሚደርስባቸው ነዋሪዎች ከፌዴራል የድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ኤጄንሲ አስቸኳይ ድጋፍ ለማያሚ እንዲደርስ ፊርማቸውን አኑረዋል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥያቄ ከቀረበላቸው እርዳታውን ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ኤጀንሲውም ወደ ፍሎሪዳ ተልኳል።

የነፍስ አድን ሠራተኞች ከውሾቻቸው ጋር በፍርስራሹ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የነፍስ አድን ሠራተኞች ከውሾቻቸው ጋር በፍርስራሹ ውስጥ