ካናዳ ኢራን በቸልተኝነት የመንገደኞች አውሮፕላንን መትታ መጣሏን አመለከተ

በአደጋው ቤተሰቦቻቸው የሞቱባቸው ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, 138 ከካናዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች በሞቱበት አደጋው ቤተሰቦቻቸው ያጡ ሰዎች

የዩክሬን ጄት ተመትቶ መጣሉን አስመልክቶ በካናዳ መንግሥት የቀረበ አንድ ሪፖርት ጉዳዩ "አስቀድሞ የታቀደ" መሆኑን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ ባያገኝም ኢራን ግን "ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ናት" ብሏል።

የዩክሬን ኢንተርናሽናል አየር መንገድ በረራ ቁጥር ፒኤስ752 እአአ ጥር 8/2020 ከቴህራን ከተነሳ በኋላ በሁለት ሚሳኤሎች ተመትቶ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 176 ሰዎች በሙሉ ህይወታቸው አልፏል።

ገለልተኛ ምርመራዎችን በማስተጓጎል የተከሰሰችው ኢራን አውሮፕላኖቹን የመታችው የአሜሪካ ሚሳኤል ነው በሚል በተፈጠረ ስህተት መሆኑን ገልጻለች።

በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት መካከል 138 የሚሆኑት ከካናዳ ጋር ግንኙነት ነበራቸው።

ዩክሬን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አፍጋኒስታን እና ስዊድን ዜጎች ህይወትም አልፏል።

ጥፋቱ የኢራን "ሲቪል እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት" መሆኑን ካናዳ ሐሙስ ዕለት ገልጻለች።

የአየር መከላከያ ክፍል ኦፕሬተር "ሚሳኤሎቹን ለመተኮስ በራሱ እርምጃ ወስዶ ሊወስን እንደሚችል" ቢገነዘቡም የኢራን ባለስልጣናት "የብቃት ማነስ፣ ግዴለሽነት እና ለሰው ህይወት ቸልተኝነት ባይሆን ጥቃቱ አይደርስም ነበር" ሲል ለስምንት ወራት ሲደረግ የነበረው ምርመራ ያጠቃልላል።

የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርክ ጋርኔዩ ሐሙስ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ኢራን በምንም መልኩ ችግሩ እንዳይከሰት አልሠራችም። ለተፈጠረው ነገር ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ናት" ብለዋል።

ምርመራው እንዳስታወቀው የኢራን ፀረ-አውሮፕላን ሚሳኤሎች በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን የተገለጸ ቢሆንም ባለሥልጣናቱ የአየር ክልላቸውን አልዘጉም ወይም በወቅቱ አገልግሎት የሚሰጡ አየር መንገዶችን አላሳውቁም።

ጋርኔዩ እንዳሉት የሚሳይል አዛዡ "የማይገቡና እና ሊወገዱ የሚችሉ እጅግ በጣም የተሳሳቱ ውሳኔዎችን" አድርጓል።

የኢራን ወታደራዊ ዕዝ እና መቆጣጠሪያ ችግሩን በመፍታት እና የወደፊቱን አደጋ ለመከላከል እርምጃዎችን በመውሰድ ረገድ በጣም ዘገምተኛ ነበር ሲሉ አክለዋል።

ሪፖርቱ ማስረጃዎችን፣ አደጋው የደረሰበትን ቦታ እና ምስክሮችን ማግኘት አለመቻሉን በመግለጽ "ከኢራን ሁሉን አቀፍና ሐቀኛ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው" ባለሥልጣናቱ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢራን ባለሥልጣናት መጀመሪያ ላይ ለአደጋው ኃላፊነቱን ከመውሰድ የተቆጠቡ ሲሆን በኋላም የአደጋው ቦታ በቡልዶዘር እንዲቆፈር እና እንዲጠፋ ፈቅደዋል።

ማስረጃዎች መጨመራቸውን ተከትሎ የአገሪቱ የአብዮታዊ ዘብ የአየር ኃይል የአየር መከላከያ ክፍሉ የአሜሪካ ሚሳኤል መስሎት ቦይንግ 737-800 ን መቷል ብለዋል።

አውሮፕላኑ ከመመታቱ ከአምስት ቀናት በፊት ባግዳድ ውስጥ በአሜሪካን ሰው አልባ አውሮፕላን በተፈፀመ ጥቃት ኢራናዊው ጀነራል ቃሲም ሶሌማኒ ተገድለው ነበር።

ይኼን ተከትሎም ኢራን የአሜሪካ ጦር ኃይሎችን በሚያስተናግዱ ሁለት የኢራቅ ወታደራዊ ካምፖች ላይ ሚሳኤሎችን ተኩሳ ነበር። በዚህ ምክንያት የኢራን የአየር መከላከያ በወቅቱ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ ነበር።

መጋቢት ወር ይፋ የተደረገው የኢራን የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የመጨረሻ ሪፖርት እንደሚለው አንድ ኦፕሬተር አውሮፕላኑን "በተሳሳተ መንገድ በመለየት" ሚሳኤሎችን ያለ አዛዡ ፈቃድ ተኩሷል።

ረቡዕ ዕለት ጋርኔዩ እንዳሉት የኢራንን ዘገባ "ክፍተቶች ያሉበት" እና "ሁሉንም ጥፋቶች በመዋቅሩ ዝቅ ባሉት ሰዎች ላይ የሚያላክክ ነው" ብለዋል።

የመንግሥታቸውን የሕግ ምርመራ ቡድን በሪፖርቱ ላይ በመመርኮዝ ከኢራን "የሰው ስህተት" የሚለይ መደምደሚያ ላይ መድረስ አለመቻሉን አምነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በሰጡት መግለጫ ደግሞ "የኢራን በይፋ የተከናወነው ምርመራ ሃቀኝነት የጎደለው፣ አሳሳች እና የተፈበረከ ነው። ሆን ተብሎ ቁልፍ ጉዳዮችንም ችላ ያለ ነው" ብለዋል።

"የአገዛዙ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውሳኔ ያሳለፉ በመሆናቸው ዓለም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኙት ላይ ጣት በመቀሰር ያለምንም ቅጣት እንዲደበቁ መፍቀድ የለበትም።"

ኢራን ለተጎጂ ቤተሰቦች ካሳ እንደትከፍል የትሩዶ አስተዳደር ይፈልጋል።

በተፈጠረው ችግር ምክንያት ማዕቀብ ለመጣል ወይም ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለማቅረብ ፍላጎት እንዳለውም አመልክቷል።