በሳዑዲ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በሳምንታት ውስጥ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
የምስሉ መግለጫ, አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በሁለት ሳምንታት ወደ አገራቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት በሳዑዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ "በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተቻለ በሁለት ሳምንት ውስጥ" ምላሽ ሊያገኝ እንደሚችል ተናግረዋል።

በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙትን ዜጎች ለመመለስ እና ከአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሳዑዲ ማቅናቱን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ስለተካሄደው ምርጫ ሲናገሩ "የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ በማከናወን በዕለቱ ደም ለማፋሰስ ያቀዱ ኃይሎችን ሴራ አክሽፏል" ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አክለውም ምርጫውን የታዘቡ አካላት በቅድመ ምርጫ እና በምርጫው ዕለት የነበሩ ነገሮች ምርጫው ተዓማኒ እንደነበር እንደሚያሳዩ መመስከራቸውን ገልፀዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ምርጫው ተዓማኒና ሰላማዊ እንደነበር ማረጋገጡንም ጠቅሰዋል።

አምሳባሳደሩ በምርጫው ወቅት እና ከምርጫ በኋላ በአገሪቱ ደም እንዲፋሰስ የሚፈልጉ ኃይሎች እንደነበሩ ተናግረዋል።

በምርጫው ዕለት የነበረውን ሂደት በርካታ አገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ሽፋን የሰጡት መሆኑንም ገልጸዋል።

"በትግራይ እንደ አዲስ የተጀመረ ጦርነት የለም" ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ "የኢትዮጵያ መንግሥት ንፁሃንን ዒላማ አያደርግም" ሲሉ ተናግረዋል።

ሰሞኑን በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ መሆናቸውንና በንጹሃን ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የሚያመለክቱ ዘገባዎች እየወጡ መሆኑን ተከትሎ ነው ምላሽ የሰጡት።

ቃል አቀባዩ አክለውም ሱዳን፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በግድቡ ጉዳይ እንዲሰበሰብ ጥያቄ ማቅረቧን በተመለከተ ሲመልሱ "አፍሪካ ሕብረት ምን አደረጋችሁ? ለምን ባሕር ማዶ ትሄዳላችሁ? ነው መልሳችን" ብለዋል።

የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ግድቡ በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመወያየት በተቻለ ፍጥነት ስብሰባ እንዲያካሄድ ጠይቆ ነበር።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ግን "ጥያቄው ተገቢ ያልሆነና ለአፍሪካ ሕብረት ጥረት ክብር የማይሰጥ ነው" ሲሉ ገልጸውታል።

በተጨማሪም ሱዳን በአብዬ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲወጣላት ጥያቄ ስለማቅረቧ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ሰላም አስከባሪ የማስገባትና የማስወጣት ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊነት እንጂ የሌላ አካል አለመሆኑን አስታውቀዋል።