በትግራይ ተፈጸመ በተባለ 'የአየር ጥቃት' በርካቶች መጎዳታቸው ተገለጸ

በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎች ለህክምና የተወሰዱበት መቀለ የሚገኘው የአይደር ሆስፒታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎች ለህክምና የተወሰዱበት መቀለ የሚገኘው የአይደር ሆስፒታል

ትግራይ ውስጥ ከመቀለ 25 ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው ቶጎጋ በተባለች ቦታ ላይ ተፈጸመ በተባለ የአየር ጥቃት በርካታ ሰዎች መሞታቸውንና መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

አንድ የሐኪም ደግሞ በአየር ጥቃቱ 43 ሰዎች መቁሰላቸውን ለሮይተርስ የዜና ወኪል የተናገረ ሲሆን የሞቱ ሰዎች ስለመኖራቸው የገለጸው ነገር የለም።

የዓይን እማኞች ቶጎጋ በሚባል አካባቢ በገበያ ስፍራ የተፈጸመው ጥቃት በኢትዮጵያ አየር ኃይል እንደሆነ ቢናገሩም ሠራዊቱ ግን የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጎታል።

"የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው በሽብርተኛ ቡድኑ አባላት ላይ እንጂ፣ በሠላማዊ ሰዎች ላይ አይደለም" ሲሉ የሠራዊቱ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ተናግረዋል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን "ሽብርተኛ" ድርጅት ብሎ መሰየሙ ይታወሳል።

በአይደር ሆስፒታል የሚገኝና በጥቃቱ እጁ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት የተገለጸ አንድ ግለሰብ እንዳለው በጥቃቱ ወቅት በርካታ ሰዎች በዙሪያው ወድቀው መመልከቱን ጠቅሶ አንድ የሚያውቀው ስውም መሞቱን ተናግሯል።

የመቁሰል ጉዳት ደርሶባት ሆስፒታሉ ውስጥ ያለች አንዲት ሴት በተመሳሳይ እንደተናገረችው ከአየር ጥቃቱ በኋላ የነበረው ሁኔታ የተመሰቃቀለ እንደነበረና "በርካታ የሞቱ ሰዎች ወድቀው" መመልከቷን ገልጻለች።

ወደ ሆስፒታሉ የመጡ ሰባት የቆሰሉ ሰዎችን እያከመ እንደሆነ የተናገረና ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ አንድ ሐኪም እንዳለው፤ ክስተቱ ወዳጋጠመበት ቦታ በመሄድ እርዳታ እንዳያደርጉ ሐኪሞች ተከልክለዋል ብሏል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት "በገበያ ቦታ ላይ ፈጽሞ የአየር ጥቃት አልፈጸምንም። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሠራዊቱ ኢላማውን በትክክል የመምታት አቅም አለው" ብለዋል።

ጨምረውም "የአየር ጥቃቶችን ፈጽመናል ነገር ግን በተመረጡ ውስን ኢላማዎች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። ስለዚህ በገበያ ስፍራ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል የተባለው ሙሉ ለሙሉ ውሸት ነው" ሲሉ ክሱን ውድቅ አድርገውታል።

ባለፉት ቀናት ከመቀለ በስተሰሜን ያለው መንገድ ለሁለት ቀናት ተዘግቶ እንደቆየ የአዲግራት ከተማ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሠራዊት ወደ ከተማዋ ከመመለሳቸው በፊት የአማጺያኑ ኃይሎች ማክሰኞ ጠዋት ላይ ወደ አዲግራት ከተማ ገብተው ነበር ተብሏል።

ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከመቀለ በስተሰሜን በሚገኝ ስፍራ ላይ ውጊያ መካሄዱን አመልክተዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የዓይን እማኞች ጨምረውም ከሥልጣን የተባረረው ክልሉን ሲመራ የነበረው የህወሓት ኃይሎች የኢትዮጵያ ሠራዊት ለቋቸው ወደ ሄደባቸው ከተሞች መግባታቸውን ገልጸዋል።

በትግራይ ውስጥ ለሚካሄደው ግጭት የህወሓት ኃይሎች የፌደራል መንግሥትን ሠራዊት የሠሜን ዕዝ አባላት በተኙበት በማጥቃት በወሰዱት እርምጃ መንግሥታቸው ወታደራዊ ምላሽ ለመስጠት መገደዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በወቅቱ መግለጻቸው ይታወሳል።

ከስምንት ወራት በፊት በተቀሰቀሰው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ሚሊዮኖች ደግሞ ተፈናቅለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከ350 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።