ትግራይ ውስጥ ከባድ ውጊያ መካሄዱ ተነገረ

የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት በታንክ ላይ ሆነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሰሜናዊ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች ውስጥ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና በአማጺያን መካከል ከባድ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ሪፖርቶች አመለከቱ።

እራሱን የትግራይ መከላከያ ኃይል ብሎ የሚጠራው ኃይል በርካታ የክልሉን ከተሞችን መያዙን የገለጸ ሲሆን፣ የአይን እማኞችም ተዋጊዎቹ በአካባቢያቸው ሲንቀሳቀሱ ማየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት ግን ቡድኑ አገኘሁ ያለውን ድል ሐሰተኛ ዜና ሲል አጣጥሎታል።

ባለፈው ጥቅምት ወር የተቀሰቀሰው ውጊያ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ በድል መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንግሥት ካሳወቀ በኋላ የአሁኑ ውጊያ እጅግ ከባዱ መሆኑ ተነግሯል።

ከስምንት ወራት በፊት በተቀሰቀሰው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ሚሊዮኖች ደግሞ ለመፈናቀል መዳረጋቸውን የረድኤት ድርጅቶች ሪፖርት ያመለክታል።

ጦርነቱን ተከትሎ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች የምግብ እርዳታን ለመጠበቅ የተገደዱ ሲሆን ከ350,000 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በረሃብ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ በተባበሩት መንግሥታት ስር የተደረገ ግምገማ ተገምቷል።

በትግራይ ክልል ውስጥ ውጊያ መቀስቀሱ የተነገረው በቀሪው የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ምርጫ ተደርጎ የድምጽ ቆጠራ እየተካሄደ ባለበት ጊዜ ነው። ባለው የጸጥታ ሁኔታ በትግራይ ውስጥ ምርጫ አልተካሄደም።

የአማጺው ቡድን ቃል አቀባይ ገብረ ገብረ ጻድቅ እንደተናገረው በርካታ ከተሞችን ኢላማ በማድረግ ጥቃት መፈጸም የጀመሩት ባለፈው ሳምንት ነው። በዚህም ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ማውደማቸውንና ወታደሮችን መማረካቸውን ገልጿል።

አማጺያኑ ከኤርትራ ድንበር በ45 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ወደምትገኘው አዲግራት ከተማ መግባታቸውን የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይህ የሚረጋገጥ ከሆነ ግጭቱ ከጀመረ በኋላ አማጺው ኃይል ያገኘው ከፍተኛው ድል ይሆናል።

የአማጺው ተዋጊዎች ከክልሉ ዋና ከተማ ውጪ በሰሜንና በደቡብ ባሉ አካባቢዎች በሚገኙ በርካታ ስፍራዎች ላይ መታየታቸውም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ የሆኑት ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ከባድ ውጊያ እንደነበረ አረጋግጠው፤ አማጺያኑ ከተሞችን፣ የጦር መሳሪያዎችን ወይም ወታደሮችን ማርከናል ያሉትን ሐሰት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

"የኢትዮጵያ መንግሥት ምርጫ በማካሄድና በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ሥራ በበዛበት ጊዜ ሽብርኛው ህወሓት፣ ታዳጊዎችን በማሰለፍ በሽብር ተግባራት ላይ ተሰማርቶ ነበር" ብለዋል ኮሎኔሉ።

የተካሄደው ዘመቻ የአማጺውን ቡድን መሪዎች ለመያዝ ነበርም ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጥቂት ወራት በፊት የቀድሞውን የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ ህወሓትን ሽብርተኛ ቡድን ብሎ መሰየሙ ይታወሳል።

በባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ መንግሥት ከኤርትራ ወታደሮች ጋር በመሆን በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ፣ የክልሉ ገዢ ፓርቲ የነበረውን ህወሓት ከስልጣኑ አስወግዶ አሸናፊ መሆኑን ማወጁ ይታወሳል።

ከወታደራዊ ግጭቱ ቀደም ብሎ ህወሓት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚያካሂዱት የፖለቲካ ለውጥ አንጻር ከፍተኛ አለመግባባት ውስጥ ገብቶ የነበረ ሲሆን በሰሜን ዕዝ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ለግጭቱ መጀመር ምክንያት ሆኗል።

ሰኞ ዕለት በተካሄደው ምርጫ ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ ለቢቢሲ በሰጡት አጭር ቃለ ምልልስ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንደተናገሩት፤ የኤርትራ ወታደሮች እንዲወጡ እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተው ነገር ግን "ገፍተው" እንደማያስወጧቸው አመልከተዋል።

የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ውስጥ ጭፍጨፋዎችን፣ መጠነ ሰፊ አስገድዶ የመድፈር ድርጊቶችን እና የሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ በማገድ ይከሰሳሉ። ነገር ግን ይህንን ክስ የኤርትራ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲያስተባብል ቆይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል ውስጥ ረሃብ እንደሌለ የተናገሩ ሲሆን በክልሉ ችግር እናዳለ አምነው ቢሆንም ግን መንግሥት የሚፈታው መሆኑን ገልጸዋል።