ምርጫ 2013፡ የምሥራቃዊ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል 'ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተካሂዷል' አለ

የምሥራቃዊ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምርጫ ታዛቢዎች በአንድ የምርጫ ጣቢያ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, EASF

የምስሉ መግለጫ, የምሥራቃዊ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምርጫ ታዛቢዎች በአንድ የምርጫ ጣቢያ ውስጥ

ሰኞ ዕለት የተካሄደውን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ምርጫ የታዘበው የምሥራቃዊ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል ምርጫው ሰላማዊ እና በተረጋጋ ሁኔታ የተካሄደ ነው ሲል ገልጸ።

ይኸው ተቋም ምርጫውን ከታዘበ በኋላ ዛሬ ማክሰኞ በምርጫው ወቅት ታዘብኳቸው ያላቸውን ጉዳዮች በተመለከተ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

የምሥራቃዊ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል (ኢስተርን አፍሪካ ስታንድባይ ፎርስ) በርካታ የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን በአባልነት የያዘ ሲሆን ዋና ዓላማውም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም እና ደኅንነትን ማረጋገጥ ነው። ይህ ኃይል የጦር ሠራዊት፣ ፖሊስ እና የሲቪል አካላትን በውስጡ አቅፎ የያዘ ነው።

ኃይሉ በአምስት ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንዲሁም በድሬዳዋ እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ 28 አባላቱ ምርጫውን እንዲታዘቡ ማሰማራቱን የታዛቢ ቡድኑ መሪ አምባሳደር አበዲላህ ኦውሌድ አሊ ተናግረዋል።

የምርጫ ጣቢያዎች ዘግይቶ መከፈተ

ኃይሉ አጠቃላይ 190 የምርጫ ጣቢያዎች መታዘቡን ገልጾ 19 በመቶ የሚሆኑት ዘግይተው መከፈታቸውን አስታውቋል። ምርጫ ጣቢያዎቹ በሰዓታቸው ሳይከፈቱ የቀሩት የምርጫ ቁሳቁሶች ማድረስ እና ማደራጀት ሥራ ላይ መዘግየት በማጋጠሙ ነው ብሏል።

የምርጫ ቁሳቁስ እጥረት

ታዛቢ ኃይሉ መልከታ ባደረገባቸው አብዛኛዎቹ ጣቢያዎች በቂ የሆነ የምርጫ ቁሳቁስ ቢኖርም የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እጥረት ግን ያጋጠመባቸው ጣቢያዎች አሉ ብሏል።

የጾታ ተዋጽኦ

የምሥራቃዊ አፍሪካ ተጠባበቂ ኃይል ምርጫ ታዛቢ ልዑክ በድምጽ ሰጪዎች ዘንድ አጥጋቢ የሚባል የጾታ ተዋጸዕኦ ነበር ብሏል። ከምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች መካከል 34 በመቶ እንዲሁም ከአገር ውስጥ ታዛቢዎች 84 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ብሏል።

ድምጽ አሰጣጥ

ምርጫ ታዛቢ ልዑኩ በአጠቃላይ በተመለከታቸው በበርካታ የአገሪቷ ክፍል የድምጽ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ሰላማዊ እና የተረጋጋ ነበር ብሏል። በብዙዎቹ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች እና አቅመ ደካሞች ቅድሚያ ተሰጥቷል ብሏል።

የፓርቲ ወኪሎች

በአንዳንድ ስፍራዎች የፓርቲ ወኪሎች ከድምጻ ሰጪዎች ላይ ጣልቃ ሲገቡ ነበር ብሏል።

የምርጫ ቆጠራ

የድምጽ መስጫ ሰዓቱ በሚጠናቀቅበት ጊዜ በርካታ ድምጽ ለመስጠት የተሰለፉ ሰዎች እንደነበሩ ታዛቢ ቡድኑ በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። ምርጫ ቦርድ ድምጽ መስጠት የሚጠናቀቅበትን ጊዜ ወደ ምሽት 3 ሰዓት ማራዘሙ ተገቢ ቢሆንም ቁጥራቸው ከፍ ያለ ምርጫ ጣቢያዎች ይህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ የደረሳቸው ምርጫ ጣቢያቸውን ከዘጉ በኋላ ነው ብሏል።

የኮቪድ-19 ጥንቃቄ

ድምጽ ሰጪዎች ድምጽ ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ሲመጡ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ማድረጋቸውን ያስተዋለ ሲሆን የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘሮች በምርጫ ጣቢያዎች ቢኖሩም አካላዊ ርቀት ግን ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ሳይጠበቅ ቀርቷል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም መራጮች ወደ ድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ከመግባታቸው በፊት እጃቸውን ሊታጠቡበት የሚችሉበት ቦታ አልነበረም።

ማጠቃለያ

ትናንት የተካሄደው ምርጫ በአጠቃላይ ሰላማዊ እና የተረጋጋ ነበር ሲል የምሥራቃዊ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምርጫ ታዛቢ ቡድን የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ገልጿል።

ምርጫ 2013