ምርጫ 2013፡ በሰሜን ጎንደር በምርጫ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት አንድ ፖሊስ ተገደለ

በሰሜን ጎንደር ዞን፣ ዳባት ወረዳ ሰኞ ዕለት ታጣቂዎች በምርጫ ጣቢያ ላይ በከፈቱት ተኩስ አንድ የፖሊስ አባል መገደሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አስታወቁ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ይህንን የገለጹት በምርጫው ዕለት ስለነበረውን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በሰጡት መግለጫ ላይ ነው።
ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ወደ ምርጫ ጣቢያው በመሄድ በስፍራው የነበሩ የጸጥታ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ ለማስገደድ መሞከራቸውንና በወቅቱ በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ አንድ የፖሊስ አባል ሲገደል ሌላ ፖሊስ ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶበታል።
ኮሚሽነሩ ጥቃቱን ስለፈጸሙት ታጣቂዎች ማንነትና ቁጥራቸው በተመለከተ ያሉት ነገር የሌለ ሲሆን፤ ዝርዝሩ በቀጣይ ምርመራ የሚጣራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከታጣቂዎችም በኩል ደግሞ አንድ ግለሰብ በተኩስ ልውውጡ መካከል መሞቱ ተነግሯል። "ሌላ ግለሰብም ቆስሎ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ በደረሰኝ መረጃ ይኽው ቆስሎ የነበረ ታጣቂም መሞቱን መረጃ ደርሶኛል" ብለዋል ኮሚሽነሩ።
ጨምረውም ከዚህ ጥቃት ውጪ ምርጫው ያለምንም የጸጥታ ስጋት መጠናቀቁን በመግለጽ "የጸጥታ ኃይሎች ለከፈሉት መስዋዕትነት" ምስጋና አቅርበዋል።
በዛሬው መግለጫቸው በአማራ ክልል ለምርጫው ብቻ ከ16 ሺህ በላይ የፖሊስ አባላት ተሰማርተው እንደነበር ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ተናግረዋል።
ይህ ቁጥር በምርጫ ጣቢያዎች ብቻ የተሰማራውን የሚመለከት አሐዝ ሲሆን ከምርጫ ጣቢያዎች ውጪ በቋሚና ተንቀሳቃሽ ጥበቃ ተግባር ላይ የተሰማሩት ሲጨመሩ ከዚህም በላይ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ፣ በምርጫው ወቅት ተስተውለዋል ያሏቸውን ጥቃቅን ግደፈቶች ሲያብራሩ በምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም መንዝ ቀበሌ ላይ የምርጫ ቁሳቁስ ባለበት አካባቢ ዋና አስተዳዳሪው የፀጥታ ኃይሎችን እራት ልጋብዛችሁ በማለት ከስፍራው ዞር እንዲሉ ካደረገ በኋላ የምርጫ ቁሳቁስ የተቀመጠበትን ቤት በመክፈት ቁሳቁሱን ከውሃ ጉዳጓድ ውስጥ ጨምሮ መሰወሩን ተናግረዋል።
በዚሁ ግለሰብ ላይ በተደረገ ክትትል ሊቀመንበሩ ከተሰወረበት መያዙን እና የምርጫ ቁሳቁሶቹ ከጉድጓድ ወጥተው ምርጫው በሰላም መከናወኑን አብራርተዋል።
አስተዳዳሪው በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት መቅረቡን የገለጹት ኮሚሽነሩ የተሰጠውን ኃላፊነቱን በአግባቡ ያልተወጣው የፖሊስ ባልደረባም በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።
በክልሉ ከሚገኙ 15 ዞኖች መካከል በዘጠኝ ዞኖች ውስጥ ከ15 እስከ 20 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ባልተፈቀደበት ጊዜና አካባቢ ሲቀሰቅሱ የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት፣ ብልጽግናን ጨምሮ፣ በቁጥጥር ስር የዋሉ መኖራቸውንም ተናግረዋል።
አንዳንዱ ሦስት አራት የምርጫ ካርድ ይዞ መገኘቱን፣ ሌሎች ምርጫ ለመምረጥ የተሰበሰቡ ሰዎች ጋር ቅስቀሳ ሲያደርጉና የቅስቀሳ ወረቀት የበተኑ መያዛቸውን እና ወደ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ለመራጭነት ተመዝግቦ የነበረ ሲሆን ትናንት በተደረገው ምርጫ የድምጽ ቆጠራ እየተጠናቀቀ ውጤት በምርጫ ጣቢያ ደረጃ እየተገለጸ ይገኛል።
ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የተካሄደው ምርጫ የጎላ የጸጥታ ችግር ሳያጋጥመው በሰላም መፈጸሙን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ምሽት አስታውቋል።













