አዲስ አይነት የሰው ዝርያ ቅሪተ አካል በእስራኤል ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, AVI LEVIN AND ILAN THEILER, SACKLER FACULTY OF MED
በእስራኤል ያሉ ተመራማሪዎች ከ 100 ሺህ ዓመታት በፊት ይኖር የነበረ እስካሁን የማይታወቅ የጥንት ሰው ዝርያ ቅሪት አገኙ።
በራምላ ከተማ አቅራቢያ የተገኙት ቅሪቶች እጅግ ጥንታዊ የሆነው አንድ የሰው ልጅ ቡድን የመጨረሻ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ይወክላሉ ሲሉ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።
ቅሪቶቹ ከ140,000 እስከ 120,000 ዓመታት በፊት የኖሩ አንድ ሰው ከፊል የራስ ቅል እና መንጋጋን ይዘዋል። የግኝቱ ዝርዝር በሳይንስ መጽሔት ውስጥ ታትሞ ተሰራጭቷል።
የተመራማሪ ቡድነ አባላቱ ግለሰቡ በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ከነበሩ ቀደምት ዝርያዎች የተገኘ እና ከአካባቢው ተነስቶ አውሮፓ ውስጥ ለሚገኙ ኒያንደርታሎች እና በእስያ ለሚገኙ ተመሳሳይ አቻዎቻቸው መነሻ ሊሆኑ ከሚችሉ ቀደምት ዝርያዎች መካከል ነው ብለው ያምናሉ።
የሳይንስ ሊቃውንቱ አዲስ ያገኙትን ዝርያ "የነሸር ራምላ ሆሞ ዓይነት" ሲሉም ሰይመውታል። የቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ሂላ ሜይ ግኝቱ የሰው ልጅ የዝግመተ ለውጥ ታሪክን በተለይም የኒያንደርታል ታሪክን ይለውጣል።
የኒያንደርታል ዝግመተ ለውጥ አጠቃላይ ምስል ቀደም ሲል ከአውሮፓ ጋር እጅግ ተቆራኝቶ ቆይቷል።
"ሁሉም ነገር የተጀመረው በእስራኤል ነው። እኛ የጠቆምነው በአካባቢው የሚኖር አንድ ቡድን የሕዝቡ መነሻ ምንጭ መሆኑን ነው" ሲሉም ተመራማሪዋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በዚያ ዘመን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኔዘር ራምላ ሕዝብ ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ አውሮፓ ተሰዷል" ሲሉም አክለዋል።
ተመራማሪዎቹ የኔዘር ራምላ ሆሞ ቡድን አባላት ቀደም ሲል ከ400,000 ዓመታት በፊት በቅርብ ምሥራቅ አካባቢ ይኖሩ እንደነበረም ደምድሟል። እንዲሁም አዲሱ ግኝት እና በአውሮፓ ውስጥ ባሉ ጥንታዊ ቅድመ ኒያንደርታል ቡድኖች መካከል መመሳሰሎችን አስተውሏል።
"ለመጀመሪያ ጊዜ በሌቫን ውስጥ የሚገኙ በተለያዩ ናሙናዎች መካከል ያሉ ነጥቦችን ማገናኘት ችለናል" ሲሉ የቴል አቪቭ ዩኒቨርስቲዋ ዶ/ር ራሄል ሳሪግ ተናግረዋል።
"እስከ አሁን በአንድ በተለየ የሰው ልጆች የዝርያ ቡድን ልንመድባቸው ያልቻልናቸው የሰው ልጆች ቅሪተ አካላት ከቀሰም፣ ከዙቲየህ እና ከታን ዋሻዎች ውስጥ ተገኝተዋል" ሲሉ አክለዋል።
"ግን ቅርጻ ቅርጾቻቸውን ኔዘር ራምላ ጋር ስናነፃፅረው በዚህ አዲስ በተገኘው ቡድን ውስጥ ማጠቃለል ስሜት ይሰጣል›› ብለዋል።
ዶ/ር ሜይ እነዚህ ሰዎች የኒያንደርታል ቅድመ አያቶች እንደሆኑ ጠቁመው የአውሮፓው ኒያንደርታል በርግጥም በሊቫንት ውስጥ ተጀምሮ ከሌሎች የሰዎች ቡድኖች ጋር በመተባበር ወደ አውሮፓ ተሰዷል ሲሉ አብራርተዋል።
ሌሎች ደግሞ ወደ ምሥራቅ ሕንድ እና ቻይና ተጉዘዋል ያሉት ደግሞ ፕሮፌሰር እስራኤል ሄርኮቭዝዝ በምሥራቅ እስያ ጥንታዊ የሰው ልጆች እና በአውሮፓ ውስጥ በኒያንደርታል መካከል ግንኙነት እንዳለ ጠቁመዋል።
"በምሥራቅ እስያ የተገኙ አንዳንድ ቅሪቶች ልክ እንደ ኔዘር ራምላ ሁሉ የኒያንደርታል ባህሪያትን አሳይተዋል" ሲሉም አክለዋል።












