በአውሮፓ እግር ኳስ ከሜዳው ውጪ ግብ ያስቆጠረ የሚለው ሕግ እንዲቀር ተወሰነ

ፖርቶ ከሜዳው ውጪ ባስቆጠረው ግብ ጁቬንቱስን ያሸነፈበት የሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፖርቶ ከሜዳው ውጪ ባስቆጠረው ግብ ጁቬንቱስን ያሸነፈበት የሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ

በአውሮፓ የክለቦች ውድድር ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው ከሜዳ ውጪ ግብ ያስቆጠረ የሚለው ሕግ ከሚቀጥለው የውድድር ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ እንደሚቀር የአህጉሪቱ የእግር ኳስ አስተዳደር ዩኤፋ ገለጸ።

እአአ ከ1965 ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ በቆየው ሕግ መሠረት ሁለት ቡድኖች በደርሶ መልስ ጨዋታ እኩል ጎሎችን ካስቆጠሩ ከሜዳው ውጪ ብዙ ጎል ያስቆጠረው ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲያልፍ ይደረግ ነበረ።

በአዲሱ ሕግ መሠረት ሁለት ቡድኖች በደርሶ መልስ ጨዋታ አቻ ከሆኑ ወደ ተጨማሪ ሰዓት እንዲያመሩ ይህ ካልሆነም ወደ መለያ ምት እንዲያቀኑ ይደረጋል ተብሏል።

የአውሮፓ እግር ኳስ የበላይ አካል ዩኤፋ ፕሬዝዳንት አሌክሳንድር ሴፌሪን "ከሜዳ ውጪ ያገባ የሚለው ሕግ ከእንግዲህ የበለጠ ክብደት እንዲኖረው ማድረግ ተገቢ አይደለም" ብለዋል።

የዩኤፋ የክለብ ውድድሮች ኮሚቴ ሃሳቡን በግንቦት ወር ላይ ያቀረበ ሲሆን አሁን በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጸድቋል።

የቀድሞው ሕግ በሻምፒዮንስ ሊግ፣ በዩሮፓ ሊግ፣ በዩሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ እና በሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች ላይ ተግባራዊ አይደረግም ማለት ነው።

ዩኤፋ እንደሚለው አዲሱ ውሳኔ በአውሮፓ ውድድሮች ላይ በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ ሚደረግ ማሸነፍን እና ጎል ማስቆጠር ያለውን ልዩነትን ያጠበዋል።

ለዚህ ደግሞ የሜዳ ጥራት፣ የተሻሻለ የስታዲየም መሠረተ ልማት እና እንደ ቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት (ቫር) ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች በምክንያትነት ይነሳሉ ብሏል።

"የሕጉ ተጽእኖ ከመጀመሪያ ዓላማው ጋር የሚጋጭ ነው ተብሏል። በሜዳቸው የሚጫወቱ ቡድኖች በተለይም በመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ወቅት ተጋጣሚዎቻቸው ጎል እንዳያስቆጥሩባቸው በመስጋት ከማጥቃት ይልቅ ወደ መከላከሉ እንዲያዘነብሉ ይሆናሉ" ብሏል።

"በተለይ ደግሞ በተጨማሪ ሰዓት ከሜዳ ውጪ የሚጫወተው ቡድን ጎል ሲያስቆጥር ባለሜዳው ሁለት ጎሎችን እንዲያስቆጥር በማስገደድ አድልዎ ይፈጥራል" ሲልም የቀድሞውን ደንብ ተችቷል።

"ስለዚህ በሜዳ መጫወት እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ አሁን አስፈላጊ አይደለም" ብሏል።

አያክስ ከቶተንሃም (እአአ በ2019)፣ ማንቸስተር ሲቲ ከቶተንሃም (እአአ በ2019)፣ ፓሪስ ሴንትዠርሜን ከማንቸስተር ዩናይትድ (እአአ በ2019) እና ሮማ ከባርሴሎና (እአአ በ2018) በቅርብ ዓመታት ከሜዳ ውጭ ግብ ያስቆጠረ በሚለው ሕግ መሠረት ውጤታቸው ከተለዩ የቅርብ ጊዜ ጨዋታዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

ፈርናንዶ ሎሬንቴ በሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ለቶተንሃም ግብ ባስቆጠረበት ወቅትg

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፈርናንዶ ሎሬንቴ በሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ለቶተንሃም ግብ ባስቆጠረበት ወቅት