ምርጫ 2013፡ የምርጫ ውጤት በምርጫ ክልል ደረጃ ረቡዕና ሐሙስ ይገለጻል ተባለ

ሰኞ ዕለት የተካሄደው ምርጫ ውጤት በምርጫ ክልል ደረጃ ረቡዕና ሐሙስ ይፋ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ቆጠራ በተጠናቀቀባቸው ምርጫ ጣቢዎች ውጤቶች ከማክሰኞ ንጋት ጀምሮ ይፋ ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን፤ የምርጫ ጣቢያ ውጤቶች ወደ ምርጫ ክልሎች ከተላኩ በኋላ "ነገ [ረቡእ] እና ከነገ ወዲያ [ሐሙስ] የምርጫ ክልል ውጤት ይፋ ይደረጋል" ሲሉ የቦርዱ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ተናግረዋል።
የምርጫ ክልል ውጤቶች ደግሞ ከመላው አገሪቱ ወደ ማዕከል ገብተው አስፈላጊው ማጣራት ከተካሄደ በኋላ ቦርዱ አጠቃላይ ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማክሰኞ ከሰዓት በበኋላ በሰጠው መግለጫ እስከ ቀጣይ 10 ቀናት ድረስ ቢያንስ ጊዜያዊ የሆነ የአጠቃላይ የምርጫ ውጤት ይፋ አድርጋለሁ ብሏል።
ከዚህ ባሻገር የተለያዩ ግለሰቦች የምርጫ ጣቢያ ውጤቶችን በመያዝ የመጨረሻ ውጤት በማስመሰል ይፋ ከማድረግ ተግራባቸው እንዲቆጠቡ ቦርዱ ጠይቋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ በርካታ አክቲቪስቶች እና ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከአንድ ምርጫ ጣቢያ የተገኘ ውጤን መሠረት በማድረግ 'የዚህ ምርጫ ክልል አሸናፊ እከሌ ነው' እያሉ ሲውጁ ተመልክተናል ብለዋል።
የምርጫ ውጤቶችን ይፋ ማድረግ የሚችለው ምርጫ ቦርድ ብቻ መሆኑን ያስታወሱት ሶሊያና፤ መሰል ተግባራት "ተቀባይነት የሌለው እና ወንጀል ጭምር ነው" ብለዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምን ያክል ሰዎች ድምጽ ለመስጥት ወጡ የሚለው አሃዝ እስካሁን እንደሌለው በመጥቀስ በርካታ ቁጥር ያለው ሰው ግን ድምጽ ለመስጥ መውጣቱን መገንዘቡ ተገልጿል።
"በከተማም በገጠርም በርካታ ሕዝብ ድምጽ ለመስጥት ወጥቷል። ይህም በጣም አስደሳች ነበር" ብለዋል የቦርዱ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ።
ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች በተካሄደው ምርጫ የተሰጡትን ድምጾች በመቁጠር ከማክሰኞ ጠዋት ጀምሮ በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ውጤቶች ይፋ እየተደረጉ ሲሆን በበርካታ ቦታዎች ውጤቶች ታውቀዋል።
ከዚህ ባሻገር በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠሙ መስተጓጎሎች ሰኞ ዕለት ድምጽ ሳይሰጥባቸው በቀሩ አካባቢዎች ዛሬ ማክሰኞ ዕለት መራጮች ድምጽ ሰሰጡ ውለዋል።
ከምርጫው ጋር በተያያዘ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ በሆቴል ክፍላቸው ውስጥ ሕይወታቸው አልፎ ስለተገኙት አሜሪካዊ ግለሰብን በተመለከተም ቦርዱ ክስተቱን ከፖሊስ መስማቱን ተናግረዋል።
"ግለሰቡ በሆቴል ክፍላቸው ሕይወታቸው አልፎ መገኘቱን ሰምተናል። ሆቴል ክፍላቸው ወድቀው ነው የተገኙት። እጅግ አሳዛኝ አጋጣሚ ነው" ካሉ በኋላ የግለሰቡ አሟሟት ከምርጫው ጋር የተገናኘ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ሶሊያና ግለሰቡ ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢ አለመሆናቸውን ጠቅሰው በእንግድነት ከምርጫ ቦርድ ባጅ ወስደው እንደነበረ ተናግረዋል።
"የመታዘብ ሥራን የሚሰሩ አልነበሩም። ለእንግዶች የሚሰጥ ባጅ ነው የወሰዱት። ከካርተር ሴንተር ለመታዘብ የመጣ የለም" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታስቦ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደዚህ ዓመት ተሸጋግሮ በሁለት ዙሮች ምርጫው እንዲካሄድ በተወሰነው መሰረት የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ተካሂዷል።
ሁለተኛው ዙር ምርጫ በሶማሌና በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች ከሁለት ወራት በኋላ ጳጉሜ 01/2013 ዓ.ም ይካሄዳል።













