6 ሜትር ቁመና፤ 30 ሜትር ርዝማኔ ያለው የአውስትራሊያ ዳይኖሰር

የአውስትራሊያ ዳይኖሰር

የፎቶው ባለመብት, QUEENSLAND MUSEUM

አውስትራሊያ ያሉ ሳይንቲስቶች በፈረንጆቹ 2007 የተገኘው አዲስ የዳይኖሰር ዝርያ በአህጉሪቷ ከታዩት በጣም ትልቁ ነው ብለዋል።

ዘ አውስትራሎሺያን ኩፐርነሲስ አሊያም ዘ ሳውዘርን ታይታን የተሰኘው ዳይኖሰር በዓለማችን ከተገኙ 15 ግዙፍ ዳይኖሰሮች አንዱ ነው።

ተመራማሪዎች ይህ ቲታኖሰር በቁመት 6.5 ሜትር በስፋት ደግሞ 30 ሜትር ይሆናል ይላሉ።

ይህ ልኬት ወደ መሬት ቢወርድ ዳይኖሰሩ አንድ ደንበኛ የቅርጫት ኳስ ሜዳን አክሎ ቁጭ ይላል ማለት ነው።

የዳይኖሰሩ አጥንት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ደቡብ ምዕራብ ክዊንስላንድ ውስጥ ካለ አንድ እርሻ ላይ ነው።

ፓሌዎንቶሎጂስቶች ባለፉት 10 ዓመታት የዳይኖሰሩን ዝርያ ለመለየት ደፋ ቀና ሲሉ ከርመዋል። ዓላማቸው ይህ ዳይኖሰር ከሌሎቹ ምንኛ ይለያል የሚለውን መለየት ነበር።

ሳይንቲስቶቹ ያገኙት ቅልጥም ራዥ እያነሱ ቁመትና ወርዱን ሲለዩ እንዲሁም ከየትኛው ዘር ነው የመጣው የሚለውን ሲያጠኑ ነበር።

ይህ ግዙፍ ዳይኖሰር ቅጠል በል ነበር። እንደ ብዙዎቹ ቅጠል በል ዳይኖሰሮች ግዝፈቱ ወደር የለውም።

እኒህ የዳይኖሰር ዝርያዎች ከሰውነታቸው ሲነፃፀር አነስ ያለ ጭንቅላት አላቸው፤ አንገታቸው ደግሞ ረዘም ያለ ነው፤ ጭራቸውም ተልክቶ የሚያልቅ አይመስልም፤ እግራቸው ወፈር ያለ ነው።

ዳይኖሰሮች በአህጉረ አውስትራሊያ 'በክሬታሴዎስ ፒሪዬድ' ከ96 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ነበር የኖሩት ይላሉ ሳይንቲስቶች።

የተመራማሪዎቹ ቡድን ለዳይኖሰሩ ኩፐር የተሰኘው ቅፅል ስም አውጥተውለታል። ኩፐር ክሪክ የተሰኘው ሥፍራ መገኘቱን ተከትሎ ይመስላል።

ሳይንቲስቶቹ የዳይኖሰሩን ዓይነት ለመለየት በርካታ ዓመታት የፈጀባቸው ቅልጥሙ የተገኘበት ሥፍራ በጣም ራቅ ያለና ጥንቃቄን የሚሻ በመሆኑ ነው።

ነገር ግን ብዙዎቹ አጥንቶች ተሰድረው ነበር የተገኙት ይላሉ የክዊንስላንድ ሙዚዬምና የኢሮማንጋ ናቹራል ሂስትሪ ሙዚዬም ተመራማሪዎች።

የዳይኖሰሩ አጥንት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በፈረንጆቹ 2007 ኢሮማንጋ ውስጥ የአንድ ቤተሰብ እርሻ ላይ ነበር።

የእርሻ መሬቱ ባለቤቶች ከአጥኚዎቹ መካከል ሁለቱ ሮቢን እና ስቱዋርት ማኬንዚ ናቸው።

የክዊንስላንድ ክልላዊ መንግሥት አዲሱን ግኝት ለዳይኖሰር ምርምር አስተዋፅዖ የሚያበርክት ሲል አሞካሽቶታል።