ዕፅ አዘዋዋሪው በለጠፈው የአይብ ፎቶ ምክንያት በፖሊስ ተያዘ

ካርል ስቲዋርት

የፎቶው ባለመብት, Merseyside Police

በእንግሊዝ አንድ ዕፅ አዘዋዋሪ በለጠፈው የአይብ ፎቶ ምክንያት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።

ግለሰቡ ስቲልቶን የተባለውን አይብ በእጁ ይዞ የተነሳውን ፎቶ ከለጠፈ በኋላ ፖሊስ ተከታትሎ በቁጥጥር ስር ሊያውለው ችሏል።

ካርል ስቲዋርት የተባለው የ39 አመት ግለሰብ ተፈላጊው የዕፅ አዘዋዋሪ መሆኑ የታወቀው በጣት አሻራው ነው።

ግለሰቡ በበይነ መረብ የመልዕክት መላላኪያ የለጠፈውን ፎቶ የእጅ አሻራ ከመረመረ በኋላ ነው ግለሰቡን ለማደን አሰሳውን የጀመረው።

ይህ ግለሰብ ሂሮይን፣ ኮኬይን፣ ኬታሚንና ኤምዲኤምኤ የተባሉ አደንዛዥ ዕፆችን በማዘዋወርና ለተለያዩ አቅራቢዎች በማቅረብ ወንጀል 13 አመት ከስድስት ወር ተፈርዶበታል።

ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው የሊቨርፑል ክራውን ፍርድ ቤት ነው።

ካርል ከዚህም በተጨማሪ የወንጀለኞችን ንብረቶች በማዘዋወር ክስም ተፈርዶበታል።

ካርል ኢንክሮ ቻት በተባለው የመልዕክት መላላኪያ መንገድ ነበር ፎቶውን የለጠፈው ነገር ግን ፖሊስ መረጃውን በመበርበር በቁጥጥር ስር አውሎታል።

ሊ ዊልኪንሰን የተባሉት የሜርሴሳይድ ፖሊስ መርማሪ እንዳሉት ቶፊ ፎርስ በተባለ የቅፅል ስም ይጠራ እንደነበርና ከፍተኛ የሚባል የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርም ተሳታፊ ነበር።

መርማሪው እንደሚሉት "ለስቲልቶን አይብ" የነበረው ፍቅር ለመውደቂያው ምክንያት ሆኗል።

በእጁ ይዞት የነበረው የአይብ ፎቶን የጣት አሻራን በመመርመር የካርል አሻራ መሆኑን ፖሊስ ማረጋገጥ መቻሉን መርማሪው ገልፀዋል።