የአውሮፓ ሕብረት የአውሮፕላን እስርን ተከትሎ በቤላሩስ ላይ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል ተስማማ

የፎቶው ባለመብት, NEXTA
የአውሮፓ ሕብረት የቤላሩስ አየር መንገድ በአውሮፓ ሰማይ ላይ እንዳይበር ለማድረግ ውሳኔ ላይ መድረሱን አስታወቀ።
ሕብረቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው እሁድ ዕለት በበረራ ላይ የነበረ አውሮፕላን አንድ ጋዜጠኛን ለመያዝ ሲል አቅጣጫውን እንዲለውጥ ተገዶ ሚንስክ እንዲያርፍ መደረጉን ተከትሎ ነው።
በብራስልስ በተካሄደው ስብሰባ የ27ቱ አባል አገራት መሪዎች የአውሮፓ ሕብረት አየር መንገዶችም በቤላሩስ ሰማይ ላይ ድርሽ እንዳይሉ ተናግረዋል። ሕብረቱ ሌሎች ተጨማሪ ምጣኔ ሃብታዊ ማዕቀቦችን እንደሚጥልም አስታውቋል።
የ26 ዓመቱ ሮማን ፕሮታሴቪች ከግሪክ ወደ ሊቱያኒያ እየበረረ ሳለ ነበር አውሮፕላኑ ውስጥ ቦምብ ሊኖር ይችላል በሚል አውሮፕላኑ አቅጣጫውን ለውጦ ሚንስክ እንዲያርፍ የተገደደው።
ይህንን ተከትሎ ምዕራባውያን አገራት ቤላሩስን በራየንኤር አውሮፕላን ጠለፋ ከሰዋል።
አሁን ላይ የወጣ ተንቀሳቃሽ ምሥል ጋዜጠኛ ፕሮታሴቪች በምንስክ አየር ማረፊያ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ ያለ ፈቃዱና ጫና ተደርጎበት ምሥሉ መቀረጹን ያሳያል።
ሰኞ ዕለት በወጣው በዚሁ ተንቀሳቃሽ ምሥል ጋዜጠኛው በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝና በቤላሩስ ግዛት የተከሰሰበትን ወንጀል እንደሠራ ተናዟል።
ይሁን እንጅ የአገሪቷን ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ መሪን ጨምሮ የመብት ተሟጋቾች ጋዜጠኛ ፕሮታሴቪች ስህተቱን እንዲያምን ጫና ተደርጎበታል ሲሉ ተንቀሳቃሽ ምሥሉን ተችተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን የቤላሩስ ባለሥልጣናት ድርጊት "አስደንጋጭ ነው፤ በፖለቲካ ልዩነት እና በፕሬስ ነጻነት ላይ የተፈጸመ አሳፋሪ ጥቃት ነው" ብለዋል።
የጋዜጠኛ ፕሮታሴቪች አባት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ልጃቸው ድብደባ ሊፈጸምበት እንደሚችል ሰግተዋል።
አባት ድሚትሪ ፕሮታሴቪች ሰኞ ዕለት ለቢቢሲ ሲናገሩ ልጃቸው "በገዛ አገሩ ባለሥልጠናት እንዴት እንደሚያዝ በጣም ተጨንቄያለሁ" ብለዋል።
"እንደሚወጣው ተስፋ እናደርጋለን። ሁኔታው ለማሰብም ያስፈራል። ድብደባ እና እንግልት ሊደርስበት ይችላል። በጣም ነው የሰጋነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ድሚትሪ አክለውም " በጣም ደንግጠናል ፤ ተበሳጭተናልም። እንዲህ ዓይነት ነገር በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያውም በአውሮፓ እምብርት ላይ መፈፀም አይገባውም ነበር" ብለዋል።
የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ ሁሉም የዓለም ማሕበረሰብ በባለሥልጣናቱ ላይ ታይቶ የማይታወቅ ጫና እንደሚያሳድር ተስፋ አለን ብለዋል ዲሚትሪ።
ጫናውም እንደሚሰራና ባለሥልጣናቱ የሰሩት ተግባር ትልቅ ስህተት እንደሆነ እንደሚገነዘቡም ተስፋ እንደሚያደርጉ አባት ዲሚትሪ ገልጸዋል።
ጋዜጠኛው ማነው?
የ26 ዓመቱ ጋዜጠኛ ከቤላሩስ የወጣው እአአ በ2019 ነው። ኔክስታ ለተባለው መገናኛ ብዙኃን የቤላሩስም የ2020 ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ዘግቧል።
ኔክስታ በዋነኛነት በቴሌግራም የሚሠራጭ መገናኛ ብዙኃን ሲሆን፤ በትዊተር እና በዩቲዩብ ላይም ይገኛል።
በምርጫው ወቅትና ከምርጫው በኋላም የቤላሩስን የተቃውሞ ድምጽ በማሰማት ከፍተኛ ሚና አለው።
ጋዜኛው ከምርጫ ዘገባው በኋላ ቤላሩስ ከሳዋለች።
ቤላሩስ ውስጥ በሽብርተኝነት ስለተፈረጀ የሞት ቅጣት እንደሚጠብቀው ተቃዋሚዋ ስቪትና ቲካንቫክያ ተናግረዋል።
ተቃዋሚዋ በምርጫው ማሸነፋቸውን ይናገራሉ። ሆኖም ግን ከቤላሩስ መንግሥት ሸሽተው ሊቱዋንያ ለመሸሸግ ተገደዋል።












