አንድ ጋዜጠኛን ለመያዝ በረራ ላይ የነበረ አውሮፕላን እንዲያርፍ ተገደደ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከግሪክ ወደ ሊቱዋንያ እየተጓዘ የነበረ የራየንኤር አውሮፕላን ቤላሩስ አርፎ ለሰዓታት እንዲቆይ መገደዱ ተነገረ።
የመብት ተሟጋቾች እንዳሉት አውሮፕላኑ ማረፊያውን እንዲለውጥ የተደረገው በአውሮፕላኑ ተሳፍሮ የነበረ ጋዜጠኛን ለመያዝ ነው።
የአውሮፓ አገራት ድርጊቱ አስቆጥቷቸዋል። ቤላሩስን "መንግሥት የሚደግፈው ሽብር" እያራመደች ነው በሚልም ኮንነዋታል።
አውሮፕላኑ ወደ ሊቱዋንያ እንዲጓዝ የተፈቀደው ኔክስታ ግሩፕ የተባለ መገናኛ ብዙሃን የቀድሞ አርታኢ የነበረው ሮማን ፕሮቶቪች ከተያዘ በኋላ ነው።
የቤላሩስ መገናኛ ብዙሃን እንዳሉት፤ አውሮፕላኑ ውስጥ ቦንብ ሊኖር ይችላል በሚል ስጋት አውሮፕላኑ ወደ ሚንስክ ቢወሰድም ምንም ነገር አልተገኘም።
አውሮፕላኑ ሉቲዋንያ ያረፈው ሰባት ሰዓታት ዘግይቶ ነበር። አውሮፕላኑ ለምን ወደ ሚንስክ እንደተወሰደ እንዳልተነገራቸው ተሳፋሪዎች ገልጸዋል።
አንድ ተሳፋሪ ደግሞ ጋዜጠኛው ሮማን ፕሮቶቪች አውሮፕላኑ መንገድ ሲለውጥ ፈርቶ እንደነበር ተናግረዋል። "ፍርሀት ይታይበት ነበር። አይኑን ስመለከተው ያሳዝንም ነበር" ብለዋል።
ሞኒካ ሲምኪኔ የተባለች ተሳፋሪ ለኤኤፍፒ "ፊቱን ወደተሳፋሪዎቹ አዙሮ የሞት ቅጣት እንደሚጠብቀው ተናግሯል" ብላለች።
የአውሮፓ ሕብረት እና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን አገራት ጣልቃ እንዲገቡ ተጠይቀዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ዶምኒክ ራብ "ይህ ያልተገባ ድርጊት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይወስዳል" ብለዋል።
የቤላሩስ የተቃዋሚ መሪ ስቪትና ቲካንቫክያ ጋዜጠኛው እንዲለቀቅ ከጠየቁት መካከል ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ስለተፈጠረው ነገር ምን ተባለ?
ከግሪክ የተነሳው አውሮፕላን ወደ መዳረሻው ሲቃረብ ነበር መስመር ለውጦ ወደ ሚንስክ እንዲሄድ የተደረገው።
171 ተሳፋሪዎች ጭኖ ነበር።
ራየንኤር እንዳለው፤ የአውሮፕላኑ ሠራተኞች በደኅንነት ስጋት ሳቢያ አውሮፐፕላኑ እንዲያርፍ መደረጉ ተነግሯቸዋል።
ሚንስክ ውስጥ ፍተሻ ከተደረገ በኋላ ምንም አጠራጣሪ ነገር ባለመገኘቱ ወደ መዳረሻው እንዲሄድ ተወስኗል ተብሏል።
የጋዜጠኛውን መታሰር ይፋ ያደረገው 'ኔክስታ' የተባለው መገናኛ ብዙሃን ነው።
ድርጊቱ ብዙዎችን አስቆጥቷል።
በቤላሩስ የአሜሪካ አምባሳደር ጁሊ ፊሸር፤ አውሮፕላኑ ውስጥ ቦንም ተገኝቷል በሚል ውሸት ጋዜጠኛው እንዲታሰር መደረጉን ኮንነዋል።
የአውሮፓ ምክርት ቤት ኃላፊ ቻርልስ ሚሼል እንዳሉት የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ጉዳዩ ላይ ይወያያሉ። አንዳች እርምጃ እንደሚወስዱም ይጠበቃል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን አገራት ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶትልበርግ "የተፈጠረው ነገር አደገኛ እና አሳሳቢ ነው" ብለዋል።
ላቲቪያ እና ሉቲዋኒያ በቤላሩስ በኩል ማለፍ አስጊ መሆኑ ተገልጾ ዓለም አቀፍ በረራ እንዲታገድ ጠይቀዋል።
የፓላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ማቲዮዝ ሞራዊኬይ "አውሮላን መጥለፍ በመንግሥት የተደረገ ሽብርተኝነት ነው። ሊቀጡ ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል።
በአውሮፓ ታዋቂ የሆኑ የፓለቲካ ሰዎች የቤላሩስ መንግሥት ማዕቀብ እንዲጣልበት እየጠየቁ ነው።
ጋዜጠኛው ማነው?
የ26 ዓመቱ ጋዜጠኛ ከቤላሩስ የወጣው እአአ በ2019 ነው። ኔክስታ ለተባለው መገናኛ ብዙሃን የቤላሩስም የ2020 ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ዘግቧል።
ኔክስታ በዋነኛነት በቴሌግራም የሚሠራጭ መገናኛ ብዙሃን ሲሆን፤ በትዊተር እና በዩቲዩብ ላይም ይገኛል።
በምርጫው ወቅትና ከምርጫው በኋላም የቤላሩስን የተቃውሞ ድምጽ በማሰማት ከፍተኛ ሚና አለው።
ጋዜኛው ከምርጫ ዘገባው በኋላ ቤላሩስ ከሳዋለች።
ቤላሩስ ውስጥ በሽብርተኝነት ስለተፈረጀ የሞት ቅጣት እንደሚጠብቀው ተቃዋሚዋ ስቪትና ቲካንቫክያ ተናግረዋል።
ተቃዋሚዋ በምርጫው ማሸነፋቸውን ይናገራሉ። ሆኖም ግን ከቤላሩስ መንግሥት ሸሽተው ሊቱዋንያ ለመሸሸግ ተገደዋል።












