የሴቶች ጥቃት፡ በጀርመን ኢትዮጵያዊቷ ስደተኛ ከሁለት ዓመት ልጇ ጋር ተገደለች

በጀርመን የተገደሉት እናትና ልጅ [ ከግራ ወደ ቀኝ ሃይማኖት ገ/እግዚአብሔርና ሃናን ገ/እግዚአብሔር]

የፎቶው ባለመብት, WONDWESEN FANTAHUN

በጀርመን ባየርን ክሮናህ ከተማ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ አንዲት ኢትዮጵያዊት ከእነ ሁለት ዓመት ልጇ መገደሏ ተሰማ።

የሟች ሐይማኖት ገ/እግዚአብሔር የቅርብ ጓደኞች ለቢቢሲ እንደገለጹት እናትና ልጅ የተገደሉት ባለፍነው እሁድ ግንቦት 15 ቀን 2013 ዓ.ም አመሻሽ 11፡00 ሰዓት አካባቢ ነው።

እናትና ልጅን በስለት በመውጋትና በላያቸው ላይ እሳት በመለኮስ የተጠረጠረው በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኘው ሞሮኳዊ የሟች የቀድሞ የፍቅር አጋር እንደነበር ጓደኞቿ ትህትና ጸጋውና ወንድወሰን ፋንታሁን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ግለሰቡ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ በራሱም ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

በ30ዎቹ መጀመሪያ እድሜ ላይ የነበረችው ሟች ሐይማኖት ላለፉት ሰባት ዓመታት ገደማ በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ኖራለች።

በጀርመን የሚታተመው 'ፍራንክንፖስት' ዕለታዊ ጋዜጣ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዕትም የኮበርግ የወንጀል ምርመራ ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ በእናትና ልጅ ግድያ የ34 ዓመቱ ሞሮኳዊ ግለሰብ ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ ዘግቧል።

ግለሰቡ በአስጊ የጤና ሁኔታ ላይ ቢሆንም ዐቃቤ ሕግ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱን ጋዜጣው ጽፏል።

'ፍራንክንፖስት' ጋዜጣ የ31 ዓመቷ ሴትና የሁለት ዓመት ልጇ እሁድ ምሽት 11:45 በመኖሪያ ክፍላቸው ውስጥ መሞታቸውን አስነብቧል።

ጋዜጣው የኮበርግ ወንጀል ምርመራ ቡድንና ዐቃቤ ሕግን ጠቅሶ እንደዘገበው ግለሰቡ እናትና ልጅ ወደሚኖሩበት ቤት ህንጻ በማምራት በቢላ ወግቶ ሳይገላቸው እንዳልቀረ ከፍተኛ ጥርጣሬ አለ።

በወቅቱ በህንጻው ውስጥ የነበሩ ሌሎች ሦስት ሴቶች ተሯሩጠው በመውጣት ለፖሊስ እንደደወሉ ጋዜጣው ጠቅሷል። በእናት ልጅ መኖሪያ ቤት ውስጥ እሳት የተነሳውም በዚህ ጊዜ ነበር።

ግለሰቡ ሆነ ብሎ እናትና ልጅ ላይ እሳት እንደለኮሰ ፖሊስ ጥርጣሬ እንዳለው 'ፍራንክንፖስት' ዘግቧል።

የእናትና ልጅ አስክሬንም የተገኘው በእሳት አደጋ ሠራተኞች ነበር። እንደ ጋዜጣው ከሆነ ግለሰቡም በእሳቱና ከበረንዳ ላይ ዘሎ ለማምለጥ በመሞከሩ ለሕይወቱ አስጊ የሆነ ጉዳት ደርሶበታል።

የእናትና ልጅ የአስክሬን ምርመራ ውጤት የሁለት ዓመቷ ህጻን በቢላ በመወጋቷ ሕይወቷ ሲያልፍ፤ እናቷ ግን በስለቱ ጉዳት ቢደርስባትም እሳቱ ከተነሳ በኋላ ሕይወቷ ማለፉን ያሳያል ተብሏል።

የመኖሪያ ሕንጻው በእሳቱ የደረሰበት ጉዳትም በ50 ሺህ ዩሮ [ከ2 ሚሊየን 600 ሺህ ብር በላይ] እንደሚገመት ጋዜጣው አክሏል።

የቅርብ ጓደኞቿ ምን ይላሉ?

ትህትና ጸጋው የሐይማኖት የቅርብ ጓደኛ ናት። የምትኖረውም በጀርመን ባየርን ክሮናህ ከተማ ነው።

መኖሪያዋም ከስደተኞች ካምፑ 5 ደቂቃ ያህል ቢያስኬድ ነው።

ሐይማኖትና ልጇ ተገደሉ ከተባለበት ሰዓት 5 ሰዓታት ቀደም ብሎ ማለትም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ገደማ ተደዋውለዋል።

በወቅቱም ልጇን ይዛ ስትወጣ "እገልሻለሁ!" ሲል እንደዛተባት አጫውታት ነበር።

ነገር ግን እስከምታውቀው ድረስ ግለሰቡ የአዕምሮ ጤና ችግር ስለሌለበት ይህንን ይፈጽማል ብላ አላሰበችም ነበር።

"እንዲህ የከፋ ነገር ያመጣል ብዬ ስላላሰብኩ በፖሊስ የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ 'አትፍሪ! አይዞሽ!' ብዬ አጽናናኋት" ትላለች።

ከሰዓታት በኋላ የሄሊኮፕተርና የእሳት አደጋ መኪና ድምጽ ሰማች። ብቅ ብላ ተመለከተች። ሁኔታው ግራ ቢያጋባትም በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው ለማንሳት ነበር የመሰላት።

ወደ ቤት ተመልሳ ሰትገባ የጽሁፍ መልዕክቶች ደረሷት፤ "የስደተኞች ካምፕ እሳት ተነስቷል" የሚል። ወደምታውቃቸው ስልክ መታች። "ጉድ ሰራን!" የሚል መልስ መልስ ነበር ያገኘችው። በቀጥታ ወደ ሥፍራው አመራች። በቦታው ስትደርስ ፖሊሶች የእናትና ልጅን አስክሬን እያወጡ ነበር።

በጀርመን የተገደሉት እናትና ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Thitna Tsegaw

"ግለሰቡ እናትና ልጅን ቤታቸውን ሰብሮ ገብቶ በጩቤ ደረታቸው ላይ ወግቶ ነው የገደላቸው። ከዚያም እሳት ለኮሰ። ግን ሟቾቹ የመለብለብ አደጋ ነው የደረሰባቸው። እርሱም ቤንዚን አርከፍክፎ ራሱን አቃጥሏል" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ትህትና እንደምትለው ግለሰቡ የሐይማኖት የፍቅር አጋር ነበር- ለወራቶች የዘለቀ ግንኙነት ነበራቸው።

በካምፑ ውስጥ ሁለቱም ለየብቻ ነበር የሚኖሩት። እርሷ በሴቶች ክፍል፤ እርሱም በወንዶቹ። ነገር ግን ጎረቤት ነበሩ።

ግንኙነታቸው ግን አልዘለቀም። በባህልም፣ በባህርይም ልዩነት ባለመግባባታቸው ተለያዩ።

እርሱ ግን ከእርሷ ጋር መለያየት አልፈለገም።

ሁኔታው ያሰጋት ሐይማኖትም ለሕይወቷ እንደምትፈራ በተለያዩ ጊዜያት ለፖሊስ እያለቀሰች አመልክታለች።

"አልቅሼ ሳስረዳቸው የአዕምሮ ሕክምና ያስፈልግሻል ወደዚያ ሂጂ አሉኝ" በማለት በአንድ ወቅት እንደነገረቻት ጓደኛዋ ትህትና ታስታውሳለች።

እንደ ትህትና ከሆነ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ፖሊስ ጣቢያው አማርኛ ተናጋሪ አስተርጓሚ ቀጥሮ በዚሁ ጉዳይ ላይ ሁለት ሰዓታት የፈጀ መጠይቅ አድርገውላትም ነበር።

ነገረ ግን መንግሥት ቦታ ካልቀየረ በስተቀር በበግል ፍላጎት ሌላ ቦታ መሄድ ባለመቻሉ ሐይማኖት እዚያው ለመቆየት ተገድዳለች።

ትህትና እንደምትለው በግድያው የተጠረጠረው ሞሮኳዊ በቅርቡ ያቀረበው የጥገኝነት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ በሥራ ላይ ነበር።

በስደተኛ ካምፕ ውስጥ የተለያየ የአዕምሮ ጤና ችግር አሊያም የባህል ልዩነቶች ያሉባቸው ሰዎች በአንድ ላይ ስለሚኖሩ መሰል አደጋዎች እንደሚከሰቱ ትህትና ትናግራለች።

ከዚህ ቀደም አንድ አፍጋኒስታዊ መገደሉንም ታስታውሳለች።

"20 ደቂቃ በፊት ደውላልኝ ነበር"

ሌላኛው የሐይማኖት የቅርብ ጓደኛ ወንድወሰን ፋንታሁን ነዋሪነቱ በጀርመን ሙኒክ ከተማ ነው።

ትውውቃቸው ሟች ጀርመን ከገባችበት ጊዜ ይጀምራል። ላለፉት አምስት ወይም ስድስት ዓመታት የዘለቀ።

ወንድወሰን ለዓመታት በዚያው መጠለያ ካምፕ ውስጥ ነበር የሚኖረው። መጠለያ ካምፑ የገባው ከእርሷ ቀደም ብሎ ነበር። ጥሩ ጓደኛሞች ነበሩ።

ተገደለችበት ከተባለው ሰዓት 20 ደቂቃ ቀደም ብሎም ደውላለት ነበር፤ ነገር ግን መንገድ ላይ በመሆኑ ስላልተመቸው ስልኩን አላነሳውም።

ለመጨረሻ ጊዜ ግን ቅዳሜ ዕለት ነበር ያወሩት። ያለችበትን የስደተኛ ካምፕ ለመቀየር ደብዳቤ ማስገባት እንዳለባት ነበር የተመካከሩት።

ሐይማኖት ስጋት እንዳላት ለእርሱና ለሌሎች ጓደኞቿ ትነግራቸው እንደነበር የሚናገረው ወንድወሰን፤ ቦታ ለመቀየር ለፖሊስ ማመልከቻ አስገብታ በሂደት ላይ ሳለች ነው የተገደለችው ይላል።

ወንድወሰን በካምፑ የእሳት አደጋ መነሳቱን ዜና እንዳነበበና ለማጣራት ጓደኞቹ ጋር ሲደውል "ገደላቸው!" የሚል መልስ እንዳገኘ ይናገራል።

"እነርሱ እንደሆኑ አልተጠራጠርኩም ነበር። ምንም የማታውቅ የሁለት ዓመት ልጅ ግን ይህ ይደርስባታል ብዬ አልገመትኩም" ይላል ወንድወሰን።

"ሐይማኖት ለሰዎች የተሰጠች መልካም ሰው ነበረች፤ ጥሩ ጓደኛዬ ነበረች" ይላል።

ወንድወሰን ከሞሮኳዊው ግለሰብም ጋር በእርሷ አማካኝነት ትውውቅ ነበረው። "ልጁ መልካም ሰው ነበር፤ ልጇን ይንከባከባል። ግን የባህል ልዩነቶች ነበሩ። 'ሴት ሌላ ሰው ማየት የለባትም ይል ነበር' እና በመሃል 'ተቀየረብኝ' አለችኝ" ሲል የነበራቸውን ግንኙነት ያስታውሳል።

በዚህ ምክንያት ሁለቱም አብረው መኖር እንደማይችሉ ተነጋግረው ተለያይተው ነበር።

ይሁን እንጂ ግለሰቡ ከአንድም ሁለት ሦስቴ ድብደባ ፈጽሞባት እንደነበር ወንድወሰን ይናገራል።

"በመጀመሪያ ለፖሊስ ስታመለክት ፖሊሶች ልጁ አጠገቧ እንዳይደርስ ማድረግ ወይም ሌላ መፍትሔ መፈለግ ይችሉ ነበር፤ በማይገባ የፖሊሶች ቸልተኝነት እርሷንና ልጇን አሳጥቶናል" ሲል ይወቅሳል።

አሁን ጓደኞቿ የሐይማኖትንና የልጇ ሃናንን አስክሬን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ ገንዘብ እያሰባሰቡ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"ክሮናህ ትንሽ ከተማ ናት። ካምፑ ለፖሊስ ጣቢያው ቅርብ ነው። በእግርም ቶሎ የሚደረስበት ነው። ነገር ግን ፖሊሶች ከ20 ደቂቃ በኋላ እንደደረሱ ነው የሰማነው" የሚለው ወንድወሰን፤ ፖሊሶቹ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ቀጣይ ሥራቸው እንደሆነ ገልጿል።

ስለጉዳዩ በጀርመን የኢትዮጵያን ኤምባሲን ለመጠየቅ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።