አሜሪካ፡ በአውቶብስ ውስጥ ለቀናት እንዲያድሩ የተገደዱ ስደተኞች ህፃናት ጉዳይ ጥያቄን አጫረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ ለቀናት በአውቶብስ ውስጥ ተገደው እንዲያድሩ የተደረጉ ስደተኞች ህፃናት ጉዳይ ጥያቄን አጭሯል።
ስደተኞቹ ህፃናቱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት ጉዟቸውን እየጠበቁ የነበሩ ናቸው ተብሏል።
ዋይት ሃውስ ይህንን ጉዳይ "ዝም ብዬ አልመለከተውም ምርመራም እከፍታለሁ" በማለት ቃል ገብቷል።
የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፕሬስ ሴክሬታሪ ጄን ፓስኪ ሁኔታውን "በጣም አስደንጋጭ" ያሉት ሲሆን "እዚህ ደረጃ ላይ እንዴት እንደተደረሰና በምን ሁኔታም ሊፈጠር ቻለ" ለሚለውም ምላሽ እንደሚኖር ተናግረዋል።
የአሜሪካ ሚዲያዎች ሪፖርት እንዳደረጉት ህፃናቱ በአውቶብሱ ውስጥ እንደተፀዳዱና ምግብም መመገብ መቻላቸውን ነው።
በአሜሪካ ተቋማት ያሉ ስደተኞች ህፃናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።
በመጋቢት ወር 19 ሺህ ስደተኞች ህፃናት በአሜሪካ ደቡባዊ ድንበር በኩል ያለ ቤተሰቦቻቸው መግባታቸው ሪፖርት ተደርጓል።
በሚያዝያ ወር ይህ ቁጥር በትንሹም ቢሆን መሻሻል አሳይቶ ወደ 17 ሺህ 200 ህፃናት ስደተኞች ናቸው አሜሪካ የደረሱት። በዚሁ ወር 50 ሺህ የሚሆኑ ወላጆች ከስደተኞች ልጆቻቸው ጋር ወደ አሜሪካ ገብተዋል።
"ለእንዲህ አይነት ኢ-ሰብዓዊ ሁኔታ ምንም ምክንያት አያስፈልገውም" በማለት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ህፃናቱ በአውቶብስ ውስጥ ተገደው ማደራቸውን ተቀባይነት እንደሌለው አስምረዋል።
ምርመራው ከተጠናቀቀም በኋላ ቀጣዩና ኃላፊነት ሊወስድ ስለሚገባው አካል የሚወሰን እንደሆነም ጠቆም አድርገዋል።
ኤንቢሲና ዳላስ ሞርኒንግ የተባሉ የዜና ወኪሎች እንደዘገቡት ከሆንዱራስ የመጣ የ15 አመት ልጅ በዳላስ ቴክሳስ አውቶብስ ውስጥ ከቅዳሜ እስከ ረቡዕ ለአምስት ቀናት ያህል ሳይወርድ ተገዶ እንዲቆይ ተደርጓል።
ይሄም እናቱን ለማግኘት ወደ ሲያትል የሚያደርገውን ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ሲሆን ከዚያም በኋላ ረዥሙ የተባለውን 3 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዝ ነበረበት።
የአውቶብስ ኩባንያው ለኤንቢሲ የዜና ወኪል እንደተናገሩት አንዳንድ ህፃናት ጉዟቸው እስኪጀምር ለሰዓታት ያህል ቢጠብቁም አንዳንዶች ለቀናት ሳይወርዱ መዋልና ማደር መገደዳቸውን ነው።
"ይህ በፍፁም ተቀባይነት የለውም" በማለት የጤናና የሰብዓዊ አገልግሎት ፀሃፊ ሐቪየር ቤክራ ለኤንቢሲ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ግለሰቡ እንዳሉት ህፃናቱ ከስደተኞች ጣቢያ ማዕከል ከወጡ በኋላ ህፃናቱን መንከባብና ወደሚሄዱበት ማድረስ የሳቸው መስሪያ ቤት ኃላፊነት እንደሆነ ነው።












