ፕሬዝዳንት ባይደን ትራምፕ ያፀደቋቸውን ሕጎች ሰረዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጸድቀው የነበሩ የተወሰኑ አዋጆችን ሰረዙ።
ከሰረዟቸው አዋጆች መካከል ሐውልቶችን የሚያወድሙ ላይ ቅጣት የሚጥለው አዋጅ ይገኝበታል።
ትራምፕ ይህንን አዋጅ ያጸደቁት ባለፈው ዓመት ማሕበራዊ ፍትህን የሚጠይቁ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ሐውልቶችን ማበላሸት ወይንም ደግሞ መጣል ከጀመሩ በኋላ ነበር።
ባይደን ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ጀግኖችን ለማሰብ በቅርጻ ቅርጽ የተሞላ መናፈሻ ለማቆም ያቀረቡትን እቅድ አብረው ውድቅ አድርገውታል።
ከዚህም በተጨማሪ ውድቅ ካተደረጉ አዋጆች መካከል በ2019 የጤና መድን መክፈል የማይችሉ ስደተኞች ወደ አገር እንዳይገቡ የሚያግደው እና እኤአ በ2019 የጸደቀው ሕግ ይገኝበታል።
ትራምፕ በ2020 ሰኔ ወር ላይ የፌደራል መንግሥቱ "ማንኛውም ግለሰብ ሐውልቶችን የሚያወድም፣ የሚዘርፍ፣ የሚያራክስ" ከሆነ "ሙሉ በሙሉ እንዲቀጣ " የሚል አዋጅ አጽድቀው ነበር።
ይህ አዋጅ የጸደቀው የግራ ክንፍ አክራሪዎች፣ ሰልፈኞች እና መሳሪያ ያነገቱ ነውጠኞች ሪፐብሊካኑን ፕሬዝዳንትን በመደገፍ በምረጡኝ ቅስሳ ዘመቻ ወቅት ስማቸው በገነነበት ወቅት ነበር።
ይህ አዋጅ ሲጸድቅ የጆርጅ ፍሎይድን መገደል በመቃወም በርካታ ተቃዋሚ ሰልፎች የተለያዩ ጉዳዮችን ለመዘከር የቆሙ ሐውልቶችን ማጥቃታቸውን ተከትሎ ነበር።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አርብ ከሰአት ከሰረዟቸው ሕጎች መካከል በአሜሪካ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያላቸውን ሰዎችን ቅርጻ ቅርጽ በመስራት መናፈሻ ለመገንባት የሚያስችለው ሕግ ይገኝበታል።
በዚህ መናፈሻ ውስጥ እንዲካተቱ በማለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ራሳቸው የመረጧቸውታዋቂ ሰዎች አሉ።
ከእነዚህም መካከል ድምጻዊቷ ዊትኒ ሂዊስተን፣ የቅርጫት ኳስ ተጫዋቹ ኮቤ ብያንት፣ ወንጌላዊው ቢሊ ግርሃም እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ይህ መናፈሻ የት እንደሚገነባ ገና ያልተመረጠ ሲሆን ኮንግረስም ቢሆን ድጋፉን አልሰጠውም ነበር።
ባይደን ከሰረዟቸው ሕጎች መካከል ትራምፕ በ2019 ጥቅምት ወር ላይ ካፀደቋቸው ሕጎች መካከል ስደተኞች ወደ አሜሪካ ከመግባታቸው በፊት የሕክምና ወጪያቸውን መሸፈን እንደሚችሉ ማረጋገጥ አለባቸው የሚለውና ወዲያውኑ በፌደራል ዳኛ የታገደው ሕግ ይገኝበታል።
"አስተዳደሬ ጥራት ያለው እና ለሁሉም ተደራሽ የሚሆን የጤና ክብካቤ ስርዓት ለመዘርጋት ይሰራል" ያሉት ባይደን ይህ ደግሞ የአሜሪካ ዜጋ ላልሆኑት ጭምር መሆኑን በመግለጽ አዋጁን ሰርዘውታል።
አርብ እለት ባይን ከሰረዟቸው ሕጎች መካከል ትራምፕ ማህበራዊ ሚዲያን ሳንሱር ለማድረግ ያለሙበትን ሕግ እና አሜሪካ ለተለያዩ አገራት የምትደርገው እርዳታ ላይ የአሜሪካ ሕዝብ ለጋስነትን ለማሳየት በሚል እንዲገባ የተጠየቀው አርማ ይገኝበታል።












