የዙሉዋ ንግሥት ሥልጣን በጨበጡ በአንድ ወራቸው ሕይወታቸው አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደቡብ አፍሪካው የዙሉ ጎሳ ንጉሣዊ ቤተሰብ ንግሥት ሺይዌ ማንትፎምቢ ድላሚኒ ዙሉ ሥልጣን በያዙ በአንድ ወራቸው ሕይወታቸው ማለፉን ይፋ አደረገ።
የ65 ዓመቷ ንግሥት ማንትፎምቢ የዙሉ ንግሥት ሆነው የተሰየሙት ባለፈው ወር ነበር።
ንግሥቲቱ የደቡብ አፍሪካ ትልቁ ጎሳ መሪ የሆኑት የባላቸው ንጉሥ ጉድዊል ዝዌሊቲኒን ሞት ተከትሎ ነው።
የንግሥቷ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳሉት ህልፈታቸው እጅግ ያልተጠበቀ ነበር በዚህም ቤተሰቡ "ክፉኛ ተጎድቷል።"
የ11 ሚሊዮን ሕዝብ መሪ የሆኑት ንግሥት ተተኪ እስካሁን አልተሰየመም።
"ንጉሣዊው ቤተሰብ የክቡርነታችን ንግሥት ሺይዌ ማንትፎምቢ ድላሚኒ ዙሉን ማለፍ ይፋ ሲያደርግ ከታላቅ ሐዘን ጋር ነው" ይላል ልዑል ማንጎሱቱ ቡቴሌዚ ያወጡት መግለጫ።
ልዑሉ የንግሥቲቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆንም ያገለግላሉ።
ልዑሉ በመግለጫቸው ለዙሉ ሕዝብ "በዙሉ ጎሳ ምንም ዓይነት የሥልጣን ሽሚያ አይኖርም" ሲሉ አስረግጠዋል።
ንግሥት ማንትፎምቢ ወደ ሆስፒታል የገቡት ባለፈው ሳምንት ነበር።
ንግሥቲቱ ለሞት ያበቃቸው ህመም ምን እንደሆ በይፋ እንደማይታወቅ የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ማንትፎምቢ ሥልጣን የጨበጡት በፈረንጆቹ 2021 ወርሃ መጋቢት 24፤ የ72 ዓመት ባለቤታቸው ንጉሥ ዝዌሊቲኒን ሞት ተከትሎ ነበር።
ንጉሥ ዝዌሊቲኒን ሕይወታቸው ከስኳር ህመም ጋር በተያያዘ እንዳለፈ ተነግሯል።
ዝዌሊቲኒን የዙሉ ጎሳን ለ50 ዓመታት በመግዛታቸው በአፍሪካ ረዥም ዓመት የነገሱ የሚል ስያሜ ነበራቸው።
ንግሥት ማንትፎምቢ ማድላሚኒ ዙሉ ከንጉሡ ሚስቶች ሁሉ ከፍ ያለ ክብር የነበራቸው ከንጉሣዊ ቤተሰብ በመምጣታቸው ነው።
ማንትፎምቢ የኢስዋቲኒው ንጉሥ ምሳዋቲ ሦስተኛ እህት ናቸው።
የቀድሞዋ ስዋዚላንድ የአሁኗ ኤስዋቲኒ በአፍሪካ ብቸኛዋ ሙሉ በመሉ በንጉሣዊ ቤተሰብ የምትመራ አገር ናት።
ንግሥት ማንትፎምቢ ከንጉሥ ዝዌሊቲኒን ስምንት ልጆችን ወልደዋል።
ትልቁ ልጃቸው የ47 ዓመቱ ልዑል ሚሱዙሉ ሥልጣኑን ሊረከብ ይችላል የሚልግ ግምት አለ።












