የዙሉው ንጉሥ ጉድዊል ዝዌልቲኒ በ72 ዓመታቸው አረፉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የደቡብ አፍሪካው የዙሉ ንጉሥ ጉድዊል ዝዌልቲኒ በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ንጉሡ ከስኳር ጋር በተያያዘ ህመም ሆስፒታል ገብተው ህክምና ሲደረግላቸው ነበር ተብሏል።
ንጉሱ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የዙሉ ሕዝብ ባህላዊ መሪ ናቸው።
በአገሪቷ ፖለቲካዊ ጉዳዮችም ላይ ከፍተኛ ተፅእኖን ማሳረፍ የቻሉ እንደሆነም ይነገራል።
የስኳር ህመም ያለባቸው ንጉሡ በባለፈው ሳምንት ወደ ክዋዙሉ ናታል ሆስፒታል የገቡት የተለመደ ህክምና ለማድረግ እንደሆነ ተዘግቧል።
ነገር ግን ህመሙ ብሷባቸው ለሞት እንደዳረጋቸውም ተገልጿል።
የንጉሡ ጠቅላይ ሚኒስትር ከንጉሡ ህልፈተ ህይወት በኋላ መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን "በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት ላልተቋረጠ ድጋፍና ፀሎታችሁ በሙሉ ደቡብ አፍሪካውያንን እናመሰግናለን" ብለዋል።
ንጉሥ ጉድዊል ዝዌልቲኒ ከአባታቸው ሞት ከአውሮፓውያኑ 1968 ሞት በኋላ የዙሉ ኔሽን ተብሎ የሚታወቀውን ግዛት መርተዋል።
የደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አመራርን በተመለከተ ባወጣው ሕግ መሰረት ለንጉሥ ዕውቅና ይሰጣል።
ክዋ ዙሉ ናታል ግዛት ተብሎ የሚታወቀው የዙሉዎች ግዛት አስር ሚሊዮን ያህል ነዋሪዎች ይኖሩበታል።












