በእስራኤል የአይሁድ ክብረ በዓል በተፈጠረ መጨናነቅ በርካቶች ተረጋግጠው ሞቱ

የእስራኤል የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ኃላፊ ሜገን ዴቪድ በርካቶች መሞታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ቁጥሩን ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል፡፡

የፎቶው ባለመብት, EPA

በሰሜን ምሥራቅ እስራኤል በተፈጠረ መጨናነቅ በርካቶች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተነገረ፡፡

የእስራኤል የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ኃላፊ ሜገን ዴቪድ በርካቶች መሞታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ቁጥሩን ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል፡፡

ሐሬትዝ ጋዜጣ እንደዘገበው ቢያንስ 44 ሰዎች ሳይሞቱ አልቀረም፡፡ የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች የቆሰሉትን በማከም ተጠምደዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ አደጋውን ‹ከፍተኛ እልቂት› ብለው የጠሩት ሲሆን ለሟቾች ጸሎት እንደሚደርጉ ተናግረዋል፡፡

ላግ ቤ ኦማር መንፈሳዊ ፌስቲቫል የሚከበረው በሜሮን ተራራ ላይ ሲሆን ይህ ክብረ በዓል ከኮቪድ ወረርሽኝ መከሰት ወዲህ ምዕመናን በብዛት ተገኝተው ሲከበር ለመጀመርያ ጊዜ ነበር፡፡

በዐሥር ሺዎች እንደታደሙበትም ተነግሯል፡፡ ይህን አሐዝ አንዳንድ ሚዲያዎች ወደ መቶ ሺህ ያስጠጉታል፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መደበኛ መመርያዎችን ለመከተልም የሚሆን ኹኔታ እንዳልነበረ ተዘግቧል፡፡

በቦታው በተጠንቀቅ ቆመው የነበሩ አምቡላንሶች አደጋው ልክ እንደተከሰተ ለተጎጂዎች የመጀመርያ ዕርዳታ መስጠት ችለው ነበር፡፡

ወዲያውኑ ተረጋግጠው የሞቱትንም በሬሳ መጠቅለያ አድርገው ሲወስዷቸው ታይተዋል፡፡

እነዚህ የድንገተኛ አደጋ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ 38 ሰዎች በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ሁኔታ ላይ ናቸው፡፡

አደጋው እንዴት ሊፈጠር ቻለ በሚለው ጉዳይ መጀመርያ የወጡ ዘገባዎች ለበዓሉ የተዘረጋ ውቅር ተንዶ ነው የሚል የነበረ ቢሆንም ይህ ወደ ኋላ ላይ ተስተባብሏል፡፡

ባለሥልጣናት ኋላ ላይ አጣርተን አረጋገጥን ባሉት መሠረት አደጋው የደረሰው ሰዎች ሲገፋፉ በተፈጠረ የሰው ናዳ ነው፡፡

ጥቂት ከላይ የነበሩ ሰዎች የሌሎችን እግር ረግጠው ሲወድቁ አንዱ ሌላውን እየረገጠ ሺዎች ተረጋግጠው ሊሞቱ እንደቻሉ ነው አሁን ላይ ያለው መረጃ የሚያስረዳው፡፡

አንድ የዓይን እማኝ ‹ሁሉም ነገር በሽርፍራፊ ሰከንዶች ውስጥ ነው የኾነው› ሲል ለአገሬው ጋዜጦች ተናግሯል፡፡

ሌላ የዓይን እማኝ ደግሞ ቦንብ ሊፈነዳ ነው የሚል ነገር በመወራቱ ነው የሰዎች መተረማመስና መደረማመስ የተከሰተው ብሏል፡፡

በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የኦርቶዶክስ አይሁድ አማኞች የሚገኙበት ይህ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል በየዓመቱ በሜሮን ተራራ ላይ የሚከበር ሲሆን እሳት በማንደድ፣ ርችት በመለኮስ፣ በጸሎትና በውዝዋዜ የሚታጀብ ደማቅ የአይሁድ በዓል ነው፡፡

በዓሉ በሚከበርበት ሥፍራ መቶ ሺህ ሰዎች መገኘታቸውን ታይምስ ኦፍ ኢስራኤል ዘግቧል፡፡

ባለፈው ዓመት ይህ በዓል በወረርሽኙ ምክንያት በስፍራው ሳይከበር ቢያልፍም ዘንድሮ እስራኤል ከዓለም አገራት ክትባቱን በስፋት በማዳረስ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ስለተመደበች ጥብቅ መመርያዎችን ማላላቷን ተከትሎ ነው ሰዎች በአንድ ቦታ ተገኝተው እንዲያከብሩት የኾነው፡፡

የሟቾቹ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል አንዳንድ የአገሬው ጋዜጦች ተንብየዋል፡፡