ኮሮናቫይረስ፡ 'የኮቪድ-19 የመጀመሪያውን ዙር ክትባት መውሰድ ቫይረሱ እንዳይስፋፋ ያደርጋል'

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የመጀመሪያውን ዙር የኮሮናቫይረስ ክትባት መወጋት የበሽታውን ሥርጭት በግማሽ እንደሚቀንስ አንድ ጥናት አመለከተ።
የፋይዘርና የአስትራዜኔካ የመጀመሪያው ዙር ክትባት የተሰጣቸውና ከሦስት ሳምንታት በኋላ በቫይረሱ እንዲያዙ የተደረጉ ሰዎች ቫይረሱን ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፍ ዕድላቸው ዝቅ ያለ ነው ብሏ ጥናቱ።
የዩናይትድ ኪንግድ ጤና ሚኒስትር ማት ሃንኮክ የጥናቱን ውጤት "አስደናቂ ዜና" ሲሉ ገልፀውታል።
ሚኒስትሩ ሰዎች የክትባት ተራቸው ከደረሰ ሳያመነቱ ሄደው እንዲከተቡም አሳስበዋል።
በጥናቱ ላይ የተሳተፉ ሰዎች ክትባቱ ከተሰጣቸው ከ14 ቀናት በኋላ በቫይረሱ ቢጋለጡም ብዙም ምልክት አላሳዩም።
ምንም እንኳ የጥናቱ ውጤት "የሚበረታታ" ቢሆን ሰዎች ልክ ቫይረሱ እንዳለባቸው እያሰቡ መንቀሳቀስ አለባቸው ይላሉ ዶክተር ሜሪ ራምሴ።
ክትባቱ በተለይ በጋራ የሚኖሩ ሰዎች ክትባቱን ከአንድ ወደ ሌላ እንዳያስተላልፉ ፍቱን ነው ይላሉ የጤና ሙያተኞች።
የዋርዊክ ዩኒቨርሲቲ ምሁሩ ማይክ ቲልደስሊ ጥናቱ ክትባቶች ምን ያክል ውጤታማ እንደሆኑ ያሳያል፤ ሰዎች ክትባት መውሰድ እንዳለባቸውም ይጠቁማል ይላሉ።
ይህ ጥናት የኮሮናቫይረስ ክትባት ምን ያክል የወረርሽኙን ሥርጭት እየገታው እንዳለ ማሳያ ነው ተብሏል።
ጥናቱን ያሠራው 'ፐብሊክ ሄልዝ ኢንግላንድ' የተሰኘው የመንግሥት ድርጅት እንደሚለው ክትባቶች ሰዎች ተሰባስበው ለሚኖሩባቸው እንደ ማረሚያ ቤት ላሉ ቦታዎች ፍቱን ነው ይላል።
አሁን ምናልባት አስጊ የሚሆነው ነገር አዲስ ዓይነት የኮሮናቫይረስ ዝርያ ቢመጣ ክትባቱ መከላከል ይችላል ወይ የሚለው ነው።
ነገር ግን የዘርፉ ሰዎች ክትባቶቹ አዲስ ዓይነት የኮቪድ-19 ዝርያ ቢመጣ እንኳ መከላከል ያስችላሉ ይላሉ።
ክትባት ምንድነው?
ክትባት ማለት ለአንድ ኢንፌክሽን፣ በሽታ ወይም ተህዋሲ ሰውነታችን እንዲከላከል የሚዘጋጅ ጠብታ ነው። ክትባት በይዘቱ የተዳከመ የተህዋሲ ቅንጣትን የያዘ ሊሆን ይችላል።
ይህም ማለት በሽታውን፣ ቫይረሱን አሊያም ክትባቱን ነው ሰዎች የሚወጉት ማለት ነው።
ወይም ደግሞ በሽታው በሽታ እንዳያስከትል በሚያስችል ደረጃ ራሱን ለሰውነታችን ብቻ እንዲያጋልጥ አድርጎ ማንነቱን ማሳጣት ማለት ነው።
በዚህ ሂደት የሰውነታችን በሽታ ተከላካይ ሠራዊት ለጠላት ኃይል እንዳይሸነፍ፣ እጅ እንዳይሰጥ፣ እንዲነቃ፣ የማንቃት ትጥቅና ስንቅን የማቀበል ያህል ነው የክትባቱ ሁነኛ ተግባር።
ክትባት ለሕመም አያጋልጥም። ነገር ግን አንዳንድ ሰዎችን ሊያዳክማቸው፣ ወይም መጠነኛ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያደርስባቸው ይችላል።
ከእነዚህም ምልክቶች መካከል ክንድ ላይ ቁስለት ወይም ደግሞ ጊዜያዊ ትኩሳት የተለመዱ ናቸው።












