የእንግሊዝ እግር ኳስ ክለቦች ማሕበራዊ ሚድያን ጥለው ሊወጡ ነው

ትዊተር፣ ፌስቡክና ኢንስታግራም አርማዎች

የፎቶው ባለመብት, DeFodi Images

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፣ እንግሊሽ ፉትቦል ሊግ እና የሴቶች ሱፐር ሊግ ክለቦች ለአራት ቀናት ከማሕበራዊ ድር አምባዎች ራሳቸውን ሊያገሉ ነው።

ክለቦች ከዚህ ውሳኔ የደረሱት ማሕበራዊ ድር አምባዎች ላይ የሚታዩ ብዘበዛዎችና ማግለሎችን በመቃወም ነው።

አድማው የሚጀምረው ከአምስት ቀናት በኋላ ሚያዚያ 22 ነው።

የእግር ኳስ ማሕበር፣ እንዲሁም ሌሎች ይመለከተናል የሚሉ መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ ኪክ ኢት ኦፍ የተባለው ፀረ-ማግለል ድርጅት በዚህ አድማ ላይ ይሳተፋሉ።

የኪክ ኢት ኦፍ ሊቀመንበር ሳንጃይ ባንዳሪ "ይህ አድማ ምን ያክል እንደመረረን የሚያሳይ ነው" ይላሉ።

"ማሕበራዊ ድር አምባ አሁን አሁን በጣም መርዛማ ለሆኑ ብዝበዛዎች የተጋለጠ ሆኗል ።"

እኛ አንድ ላይ ሆነን ይህን አድማ የምንመታው ሥልጣኑ ላላቸው መልዕክት ለማስተላለፍ ነው። እርምጃ እንድትወስዱ እንፈልጋለን። ለውጥ እንድታመጡ እንሻለን።"

ሊቀ መንበሩ ማሕበራዊ ድር አምባዎች ፊታቸውን ደብቀው ለሚበዘብዙ ሳይሆን ለእግር ኳሱ ቤተሰቡ ነው የተመቸ ሊሆን የሚገባው ሲሉ ይሞግታሉ።

ባለፈው ዓመት የቆዳ ቀለሙን አስመልክቶ ብዝበዛ የደረሰበት የሼፊልድ ዩናይትዱ ዴቪድ ማክጎልድሪክ "ጊዜው አሁን ነው" ይላል።

"በእኔ ላይ የደረሰው በሌሎች በርካታ ተጫዋቾች ላይ ደርሷል። የሆነ ነገር ሊፈጠር ይገባዋል። የቆዳ ቀለምን መሠረት አድርጎ ጥቃት ማድረስ ለብዙዎች ቀላል ነው።"

ጎልድሪክ ትላንት [ቅዳሜ] ምሽት ከብራይተን ጋር በነበረው ጨዋታ አንድ ጎል አስቆጥሮ ቡድኑ እንዲያሸንፍ አስችሏል።

ተጫዋቹ ከግጥሚያው በኋላ በሰጠው አስተያየት "ሱፐር ሊግን በ48 ሰዓታት አስወገድን። ዘረኝነት መርታት ያቃተን ለምንድነው?" ሲል ጠይቋል።

የብራይተኑ ፈረንሳዊ አጥቂ ኒል ሞፔም በተመሳሳይ ማሕበራዊ ድር አምባው ላይ ጥቃት ደርሶበታል።

ተጫዋቹ ለስካይ ስፖርት በሰጠው ድምፅ "አድማው ትክክለኛ ነው" ሲል ተደምጧል።

"ተጫዋቾች በይነ መረብ ላይ ብዙ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ይህን መዋጋት አለብን። አሁን አንድ ላይ መሆናችን መልካም ነገር ነው።"

ክለቦችን ጨምሮ አስተዳዳሪ አካላት እንዲሁም የእግር ኳስ ዳኞች ማሕበር ከትዊተር፣ ፌስቡክና ኢንስታግራም ራሳቸውን ለአምስት ቀናት ለማግለል ተስማምተዋል።

ከሳምንታት በፊት ስዋንሲ ሲቲ የተሰኘው ቡድን ተጫዋቾቹ ላይ በደረሰው ጥቃት ምክንያት የአንድ ሳምንት አድማ አድርጎ ነበር።

ሌላኛው የቻምፒዮንሺፕ ቡድን በርሚንግሃም ሲቲና የስኮትላንዱ ሬንጀርስም ማሕበራ ድር አምባው ላይ አድማ መትተው ነበር።

የቀድሞው የአርሰናል ተጫዋች ፈረንሳዊው ቲዬሪ ሄንሪ በዘረኝነትና በሌሎች ጥቃቶች ሳቢያ ከማሕበራዊ ድር አምባዎች ራሱን ሙለ በሙሉ ማግለሉን ማስታወቁ አይዘነጋም።

ከቢቢሲ ጋር ቆይታ የነበረው የ43 ዓመቱ ሄንሪ "በቃ ማለት በቃ ነው" ሲል ተቃውሞውን ገልጿል።

ሊቨርፑል ሶስቱ ጥቁር ተጫዋቾቹ አሌክሳንደር-አርኖልድ፣ ናቢ ኬታና ሳዲዮ ማኔ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ቁጣውን መግለፁ ይታወሳል።

አድማ መቺዎች ዓላማቸው ማሕበራዊ ድር-አምባዎች ጥላቻን እንዲያስወግዱና ትምህርትም እንዲሰጡ መሆኑን በመግለጫቸው አትተዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ትላልቅ የማሕበራዊ ድር አምባ ኩባንያዎች ችግሩን መቅረፍ ካልቻሉ ቅጣት እንደሚጥል ዝቶ ነበር።

ፌስቡክ የካቲት ላይ ከበድ ያሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንዳሰበ አስታውቆ ነበር።

በፌስቡክ የሚተዳደረው ኢንስታግራም ደግሞ ባለፈው ሳምንት ተጠቃሚዎች ጓደኞቻቸው ያልሆኑ ሰዎች መልዕክት እንዳይልኩላቸው የሚያስችል መንገድ አምጥቻለሁ ብሏል።