በስፔንን 22 ሰዎችን በኮሮናቫይረስ ያስያዘው ግለሰብ ተያዘ

ማስክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በስፔን አንድ ግለሰብ ሆነ ብሎ 22 ሰዎችን በኮሮና ቫይረስ አስይዟል በሚል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ውሏል።

የ40 አመቱ ግለሰብ ከ40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ሙቀት፣ እንዲሁም ከፍተኛ ሳል ቢኖረውም ወደ ስራ ቦታ መሄዱን አላቆመም እንዲሁም የአካል እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ ቦታም አልቀረም ተብሏል።

ማጆክራ ከተባለው የስራ ቦታውም ማስኩን አውልቆ እየሳለ ለስራ ባልደረቦቹ እንደሚበክላቸውም እንደተናገረ ተገልጿል።

ይህንነም ተከትሎ አምስት የስራ ባልደረቦቹና ስፖርት ቦታ አብረውት የሚያዘወትሩ ሶስት ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የዚህ ግለሰብ አስራ አራት የቤተሰብ አባላቱ እንዲሁ በኮሮና መያዛቸው የተነገረ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ አንድ የሶስት አመት ህፃን ይገኝበታል ተብሏል።

በያዝነው ሳምንት ቅዳሜ እለት የስፔን ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ግለሰቡ ለቀናት ያህል የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን ቢያሳይም "ከስራ መቅረት አሻፈረኝ ብሏል እንዲሁም ወደቤቱ ለመሄድ እምቢተኝነት አሳይቷል" ብሏል።

አንድ ምሽት ላይ ምርመራ ቢያደርግም ውጤቱን ሳይጠብቅ በነገታው ስራው ቦታ እንዲሁም ወደ ስፖርት ማዘውተሪያው አቅንቷል ተብሏል።

የስራ ባልደረቦቹ ወደ ቤቱ እንዲሄድ ቢለምኑቱም በእምቢተኝነት መዝለቁን ፖሊስ ገልጿል። ከዚያም በተጨማሪ ማስኩን አውልቆ "ሁላችሁንም ኮሮናቫይረስ አስይዛችኋለሁ" ይል እንደነበር ተነግሯል።

ውጤቱም ፖዘቲቭ መሆኑን ተከትሎ የስራ ባልደረቦቹ መጨነቃቸውን ፖሊስ አስታውቋል። ይህ ክስተት የተፈጠረው ጥር ወር መጨረሻ ላይ መሆኑን የገለፀው ፖሊስ ግለሰቡ ኮሮናቫይረስ አስተላልፎባቸዋል የተባሉ የስራ ባልደረቦቹም ሆነ ቤተሰቦቹ ህመሙ አልፀናባቸውም ብሏል።