ኮሮናቫይረስ፡ በኢራቅ የኮቪድ-19 ሆስፒታል ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 82 ሰዎች ሞቱ

ሆስፒታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኢራቋ መዲና ባግዳድ በአንድ የኮሮናቫይረስ ህሙማንን በሚያክም ሆስፒታል ላይ በተነሳ እሳት ቢያንስ 82 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

ቅዳሜ ምሽት ኢብን ካቲብ ተብሎ በሚጠራው ሆስፒታል ላይ በተነሳው እሳት አደጋ ህይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ ከ100 በላይ ሰዎች ተጎድተዋል።

ሪፖርቶች እንደሚሉት ለእሳት አደጋው መነሻ የሆነው የኦክስጅን ጋዝ መያዣ ጋን በመፈንዳቱ ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቁ ቪዲዮዎች በርካቶች በእሳት ከተያያዘው ህንጻ ለማምለጥ እግሬ አውጭኝ እያሉ ሲሮጡና የእሳት አደጋ ሠራተኞችም እሳቱን ለማጥፋት ሲሞክሩ ታይተዋል።

የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል ካዲሚ ክስተቱን "አሰቃቂ አደጋ" ብለው የጠሩት ሲሆን የአገሪቱን ጤና ሚኒስትር ከሥራቸው አግደው የአደጋው ምክንያትን ለማወቅ አስቸኳይ ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

የኢራቅ የሲቪል መከላከያ ተብሎ የሚጠራው ዋና ኃላፊ ሜጄር ጄኔራል ካዲም ቦሃን ለአገሪቱ ሚዲያ እንደተናገሩት እሳቱ የተነሳው ጽኑ ህሙማን ታኝተው ከሚታከሙበት ክፍል ነው።

እስካሁን ድረስ ባለው የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች በሆስፒታሉ ከነበሩ 120 ህመምተኞችና አስታማሚዎች መካከል 90ዎቹን ማትረፋቸውን የአገሪቱ ሚዲያ አይኤንኤ ዘግቧል።

በባግዳድ ውስጥ ሆስፒታሉ የኮሮናቫይረስ ጽኑ ህመምተኞች የሚታከሙበት ሲሆን በወቅቱም 30 ጽኑ ህመምተኞች እንደነበሩም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ከሆስፒታሉ ያገኘውን ምንጭ ጠቅሶ ዘግቧል።

በእሳት አደጋው የተጎዱ ህሙማንና ግለሰቦች በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል በአምቡላንስ ተወስደዋል።

ሜጄር ጄኔራል ካዲም የእሳት አደጋውን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለም ተናግረዋል።

የባግዳድ አስተዳዳሪ የሆኑት መሐመድ ጃቤር የእሳት አደጋው ምናልባት በቸልተኝነት የተከሰተ ከሆነና ኃላፊነት ሊወስድ የሚገባው አካል ወደ ፍርድ እንዲቀርብ አስቸኳይ ምርመራ ሊከፈት እንደሚገባው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አድርገዋል።

መንግሥታዊው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ክስተቱን "በኮቪድ-19 የተዳከሙ ህሙማን ላይ የተፈፀመ ወንጀል" ሲል ጠርቶታል።

በዓመታት ጦርነት፣ ሙስናና ሌሎችም ቀውሶች በተዳከመችው ኢራቅ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ ጫናን ፈጥሯል።

በተለይም በያዝነው ዓመት ከየካቲት ወር ጀምሮ የኮሮናቫይረስ ህሙማን ቁጥር እየጨመረ ሲሆን በዚህ ሳምንት በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አንድ ሚሊዮን አልፏል።

ወረርሽኙ ከተከሰበት እለት ጀምሮ 1 ሚሊዮን 25 ሺህ 288 ህሙማን የተመዘገቡ ሲሆን 15 ሺህ 217 ዜጎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል ተብሏል።

አገሪቷ የክትባት ፕሮግራሟን ባለፈው ወር የጀመረች ሲሆን እስካሁን ድረስ 650 ሺህ ሰዎች መከተባቸውም ተገልጿል።