ከዓመት በኋላ በርካታ ተመልካቾች የሚታደሙባቸው የእግር ኳስ ጨዋታዎች ሊደረጉ ነው

እግር ኳስ ጨዋታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቶተንሃምና በማንችስተር ሲቲ ቡድኖች መካከል የሚደረገው የካራባኦ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በርካታ ተመልካቾችን ወደ ስታዲየም ለማስገባት ይቻል እንደሆነ ለመሞከር ስምንት ሺህ ደጋፊዎች በስታዲየም ውስጥ እንዲመለከቱት ይደረጋል ተባለ።

ሚያዚያ 17/2013 ዓ.ም በዌምብሌይ ስታዲየም እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ከሚታደሙት ስምንት ሺህ ሰዎች መካከል ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸው ትኬቶች ለሁለቱም ክለቦች ይሰጣሉ ተብሏል።

ከቡድኖቹ የተረፈው ትኬት ለአካቢው ነዋሪዎችና ለብሔራዊው ህክምና አገልግሎት ሠራተኞች ይሰጣል።

የእንግሊዝ እግር ኳስ ሊግ ሊቀመንበር የሆኑት ሪክ ፓሪ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ ተመልካቾች ወደ ስታዲየም እንዲመለሱ ለማድረግ "ወሳኝ እርምጃ ነው" ብለዋል።

ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ሚያዚያ 10/2013 ዓ.ም በሌስተር ሲቲ እና በሳውዝሃምፕተን ቡድኖች መካከል የሚካሄደው የኤፍኤ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ ደግሞ 4,000 ተመልካቾች ይገኛሉ የተባለ ሲሆን፤ ቀጥሎም በግንቦት ወር በሚካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ ላይ 21,000 ተመልካቾች ይታደማሉ።

እነዚህ ጨዋታዎች በርካታ ተመልካቾችን ለማስገባት እንደመሞከሪያ ከመሆናቸው በተጨማሪ ታዳሚዎች ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ሰነዶችንም የማረጋገጥ ሙከራ ሊደረግበት እንደሚችል ተገልጿል።

በዚህም ተመልካቾች የበሽታውን መከላከያ ክትባት ስለመውሰዳቸው፣ ተመርምረው ቫይረሱ እንደሌለባቸው ወይም የተፈጥሮ መከላከያ እንዳላቸው የሚያመለክቱ ሰነዶችን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

እነዚህ ሦስት ጨዋታዎች በርካታ ሕዝብ የሚታደምባቸውን ዝግጅቶች ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ለማስጀመር በታቀደው መሰረት "ወሳኝ ሳይንሳዊ መረጃ ለማግኘትና ምርምር ለማድረግ" ከተመረጡ ዘጠኝ ስፖርታዊ ውድድሮች መካከል ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።

የኤፍኤ የፍጻሜና የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ለዕቅዱ መሞከሪያ እንደሚሆኑ ቀደም ብሎ የተነገረ ሲሆን፤ ዛሬ ደግሞ ምን ያህል ተመልካቾች እንደሚታደሙና ከቫይረሱ ነጻ ስለመሆናቸው የሚያመለክቱ ሰነዶችን የመጠየቅ ሙከራ እንደሚደረግ ተገልጿል።

የካራባኦ ዋንጫ ጨዋታ ባለፈው የካቲት ወር ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፤ ወደ ሚያዚያ ወር የተሸጋገረው በተቻለ መጠን "በርካታ ተመልካች እንዲታደምበት" ለማድረግ በሚል ነው።

የእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ቡሊንግሐም እንደተናገሩት "በዌምብሌይ ስታዲየም ሦስት የመሞከሪያ ጨዋታዎችን በማስተናገዳችን ደስተኞች ነን፤ ደኅንነቱ የተጠበቀ የውድድር ቦታ እንደሚሆንም እንተማመናለን።

"እነዚህ ጨዋታዎችም በሙሉ ስታዲየም ለሚደረጉ ግጥሚያዎች ተመልካቹን እንዲመለስ ለማድረግ ሙከራው ወሳኝ የመጀመሪያ እርምጃ ነው" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የኮሮናቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ከመጋቢት ወር ጀምሮ እንግሊዝ ውስጥ የሚካሄዱ አብዛኞቹ የእግር ኳስ ውድድሮች በዝግ ስታዲየሞች ሲካሄዱ ቆይተዋል።