በአሜሪካዋ የፍሎሪዳ ግዛት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደነገገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ግዛት ከአንድ ፋብሪካ የሚወጣ መርዛማ ፋሳሽ የሚጠራቀምበትን ሰውሰራሽ ሐይቅ አልፎ በመውጣቱ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደነገገ።
በግዛቲቱ ታምፓ ቤይ በሚባለው አካባቢ መርዛማ ፈሳሽ አፈትልኮ በመውጣቱ ሳብያ በአቅራቢያው ከ300 በላይ በሚሆኑ ቤቶች ውስጥ የነበሩ ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ የታዘዙ ሲሆን፣ በአቅራቢያው የሚገኝ አውራ ጎዳናም እንዲዘጋ ተደርጓል።
ነዋሪዎችም በፍጥነት ቤታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ አጭር የጽሁፍ መልዕክት ማስጠንቀቂያ ተልኮላቸዋል።
ባለስልጣናት እንዳሉት 31 ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ ያረፈው የዝቃጭ ማጠራቀሚያ ሐይቅ በውስጡ ከአንድ አሮጌ የማዳበሪያ ፋብሪካ የወጣ በሚሊዮኖች ሊትር የሚገመት መርዛማ ንጥረ ነገሮች ያሉበትን ፈሳሽን አጠራቅሞ ይዞ ቆይቷል።
ፍሳሹ ሾልኮ የወጣበትን ቦታ ለመጠገን ጉድጓዱን በድንጋይና በሌሎች ቁሶች ለመድፈን አርብ ዕለት ጥረት የተደረገ ቢሆንም፤ ሳይሳካ በመቅረቱ ለነዋሪዎች ደኅንነት አስጊ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጀ በግዛቲቱ ውስጥ የተደነገገው።
የፍሎሪዳ ግዛት ገዢ ሮን ዴሳንቲስ ናቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ቅዳሜ ዕለት ነው ይፋ ያደረጉት።
በግዛቲቱ ማናቴ የተባለችውና በግብርና ሥራ የምትታወቀው አካባቢ አስተዳዳሪ የሆኑት ስኮት ሆፕስ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት መርዛማ ውሃው አካባቢውን ሊያጥለቀልቀው ይችላል የሚል ስጋት አለ።
"2.3 ሚሊዮን የሚገመት መርዛማ ፈሳሽ ውስጥ ከተጠራቀመበት ሐይቅ ወጥቶ በዙሪያው ያሉ አካባቢዎችን በደቂቃዎች ሊያጥለቀልቅ የሚችልበት እድል እንዳለ ነው እያሳወቅን ያለነው" ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ ባለሙያዎች ፍሳሹ የሚጓዝበትን መስመር ለመቆጣጠር ቦይ እያዘጋጁ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በሐይቁ ውስጥ ያለውን የውሃ መጠን ዝቅ ለማድረግ በሺዎች የሚቆጠር ፈሳሽን በመሳቢያ ሞተር በማውጣት እንዲፈስ እያደረጉ ነው ተብሏል።
ግዛቲቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገጓ የፈሳሽ መሳቢያ ሞተሮችንና ከባድ ተሽከርካሪዎችን ወደ ስፍራው ለማስማራት የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ሊቀርብ ይችላል።












