በፈጣን ጀልባዎች ከሞሮኮ ወደ ስፔን ዕጽ የሚያዘዋውር የማፊያ ቡድን ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, SPANISH CIVIL GUARD
ፈጣን ጀልባዎችን በመጠቀም ከሞሮኮ ወደ ስፔን አደንዛዥ ዕጽ የሚያዘዋውር የማፊያ ቡድን 100 አባላትን በቁጥጥር ስር መዋሉን የስፔን ፖሊስ አስታወቀ።
ግለሰቦቹ የአንድ ማፍያ ቡድን አባላት መሆናቸውንና አደንዛዥ ዕፁን በፈጣን ጀልባ በማጓጓዝ ወደ ስፔን እንደሚያሻግሩ ፖሊስ ገልጿል።
በደቡባዊ ስፔን እና ፈረንሳይ በተደረገው በዚህ አሰሳ 5,270 ኪሎ ግራም ሐሺሽ ተገኝቷል።
ይህ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን ሞንፓርሌት በመባል እንደሚታወቅ ፖሊስ በመግለጫው ላይ አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ አደንዛዥ ዕፁን ወደ ስፔን የሚያስገቡት በወንዝ በኩል ፈጣን ጀልባዎችን በመጠቀም ሲሆን ከዚያም በፍራፍሬ ማመላለሻ መኪና ውስጥ በመደበቅ ወደ ፈረንሳይ ያሸጋግሩታል።
በመቀጠልም በአውሮፓ ላሉ ደንበኞቻቸው እንደሚያከፋፍሉት ፖሊስ አስታውቋል።
አክሎም 5,040 ኪሎ ግራም ሐሺሽ እና 230 ኪሎ ግራም ማሪዋና መገኘቱም ታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, SPANISH CIVIL GUARD
ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ የወንጀል ቡድኑ እጅግ በጣም የተደራጀ የወንጀል መረብ ዘርግቶ የነበረ ሲሆን፣ ፈጣን ጀልባዎቹ ምንጊዜም ነዳጅ ተሞልተው ዝግጁ መሆናቸውን የሚከታተል፣ ሌሎች ወንጀሎችን በአንዳሉሺያ ባሕር ዳርቻ ለመፈፀም የሚያስችል መዋቅር ዘርግቶ ነበር።
ፖሊስ የቡድኑን አደረጃጀት ሲያስረዳ "አንድ ቡድን ከጉአዳልኩዊቪር ወንዝ ፈጣን ጀልባዎችን ያሰማራል፣ ሌላኛው ደግሞ ዶስ ሄርማናስ ከሚገኝ መጋዘን ወደ አውሮፓ አደንዛዥ ዕፆችን በጭነት መኪና አድርጎ ያከፋፍላል፤ ሦስተኛው ቡድን ደግሞ በላ ሊኒያ እና ማኒልቫ መካከል የጎደሉ ነገሮችን የመሙላት ሥራን ያከናውናል" ብሏል።
ፖሊስ ባደረገው አሰሳ ወቅት የውሸት ጠብመንጃዎች፣ የኤሌትሪክ ንዝረት የሚለቁ ሽጉጦች፣ የግንኙነት እና አቅጣጫ መጠቆሚያ መሳሪያዎች እንዲሁም አደንዛዥ እፁን ለማዘዋወር የሚውሉ መኪኖችን በቁጥጥር ስር አውሏል።












