ኮሮናቫይረስ፡ ሐሰተኛ ወሬ የሚያናፍሱ ከማኅበራዊ ሚዲያ እንዲታገዱ ተጠየቀ

ኮሮናቫይረስንና የፀሐይ ብርሃንን ምን አገናኛቸው?

የፎቶው ባለመብት, SOPA IMAGES

የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ፌስቡክ፣ ትዊተርና ጉግል ኮሮናቫይረስና ክትባቱን በተመለከተ አሳሳች መረጃዎችን የሚያሰራጩ 12 ሰዎች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ጫና እያሳደሩ መሆኑ ተገልጿል።

ተወካዩ ማይክ ዶይል በአሜሪካ የኮንግረስ ውይይት ላይ እነዚህ ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ያላቸው ግለሰቦች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች እንዲዘጉና ድርጅቶቹ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።

የፌስቡኩ ኃላፊ ማርክ ዙከርበርግ፣ የትዊተሩ ጃክ ዶርሲ እና የጉግሉ ሳንደር ፒንቻይ በፍጥነት እነዚህ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ተጠይቀዋል።

እስካሁን ግን በሁሉም ኃላፊዎች በኩል በጉዳዩ ላይ የተባለ ነገር የለም።

ፌስቡክ ግን በተቋም ደረጃ መሰል የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ሰዎች የድርጅቱን ሕግ ጥሰው እንደሆነ እየመረመረ እንደሆነ አስታውቋል። ትዊተርና ጉግል ግን በጉዳዩ ላይ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

በበይነ መረብ አማካይነት የሚተላለፉ የጥላቻና የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚከታተለው ተቋም ባወጣው መረጃ መሰረት በትዊተርና ፌስቡክ ብቻ 812 ሺ ከክትባቱ ጋር የተያያዙ መረጃዎች ተለቀዋል። ከነዚህ መረጃዎች መካከል 65 በመቶ የሚሆኑት የመጡት የተሳሳተ መረጃ ከሚያሰራጩት ግለሰቦች እንደሆነ ደርሼበታለው ብሏል።

''ፌስቡክ፣ ዩትዩብ፣ ኢንስታግራምና ትዊተር ላይ ያሉ ጸረ ክትባት አቀንቃኞች ከ59 ሚሊየን በላይ ተከታዮች አሏቸው። እነዚህ ግለሰቦች ማኅበራዊ ሚዲያዎቹን በመጠቀም ጸረ ክትባት የሆኑ መረጃዎችን እያሰራጩ ይገኛሉ'' ብሏል ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት ላይ።

ከ12 ግሰለቦች መካከል ሦስቱ ከተጠቀሱት የማኅበራዊ ሚዲያዎች ከአንደኛው የታገዱ ሲሆን፤ እስካሁን ከሁሉም ላይ ግን አልታገዱም።

የተሳሳተ መረጃና ጸረ ክትባት መልእክቶችን ያስተላልፋሉ ከተባሉት 12 ግለሰቦች መካከል ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር አንዱ ሲሆን የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የወንድም ልጅ ነው።

ከእሱ በተጨማሪ ዶክተር ጆሴፍ ሜርሶላ እና ቻርሊን ቦሊንገር ይገኙበታል።

12 የአሜሪካ ግዛቶች ጠቅላይ አቃቤ ሕጎች ለማርክ ዙከርበርግና ጃክ ዶርሲ ደብዳቤ ጽፈዋል። በደብዳቤያቸው እነዚህን ግለሰቦች ማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዲያግዷቸውና የተሳሳተ መረጃው እንዲቆም እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

እስካሁን የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳን ጆን ኤፍ ኬኔዲ የወንድም ልጅ የሆነው ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር ከኢንስታግራም ላይ የታገደ ሲሆን የፌስቡክ ገጹ ግን እስካሁን ይሰራል።