የአሊባባው ጃክ ማ ለሦስት ወራት ከዕይታ የጠፉት ለምንድን ነው?

ጃክ ማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጃክ ማ በቻይና ሃብታሙ ግለሰብ ለመሆን ተቃርበው ነበር፡፡

በጎርጎሮሳዊያኑ ህዳር 2020 ለሌላ የንግድ ሥራ ስኬት ደፋ ቀና በሚሉበት ዋዜማ ሃሳባቸውን በግልጽ የሚናገሩት ቢሊየነር በድንገት ጠፉ።

ኩባንያቸው አሊባባ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከሚሠራ የድረ ገጽ መደብርነት ተነስቶ በዓለም ግዙፉ ቴክኖሎጂ ለመሆን በቅቷል፡፡

ዛሬ በድረ ገጽ ግብይት፣ ክላውድ ኮምፒውቲንግ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ወደ 800 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጠቃሚዎችን ደርሷል፡፡

ተጽዕኖ ፈጣሪው እና ሃብታሙ የቴክኖሎጂው ሰው በደማቅ መድረኮች በመገኘት እና በማስተዋወቅ ይታወቃሉ፡፡

በሺዎች ለሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸው 'ፓርቲ' ይደግሳሉ። 'You Raise Me Up' ያሉ ሙዚቃዎችንም ይጫወታሉ፡፡

አዲሱ ኩባንያቸው አንት ግሩፕ በቻይና ያለውን የዲጂታል ክፍያን በአሊፔይ የሞባይል ፋይናንስ መተግበሪያ በኩል ይመራል፡፡

አወዛጋቢ ንግግር

ኩባንያው በቻይና የሚገኙ ባንኮችን በማዘመን ያላቸውን ኃይልን ከእነዚህ ነባር ተቋማት ለማሸጋገር ዓላማ አድርጎ ተነስቷል።

ጥቅምት 24 ቀን በሻንግሃይ ውስጥ አንት ግሩፕ በዓለም ላይ ትልቁን የአክሲዮን ድርሻ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ለማቅረብ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም ብሎ ግን ማ በቻይና የገንዘብ ስርዓት ላይ ትችት የሰነዘሩበትን አከራካሪ ንግግር የታወቁ ሰዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ አደረጉ፡፡

እስከ ጥር መጨረሻ ድረስም እንደገና በአደባባይ አልታዩም፡፡ ምናልባትም በቤት ውስጥ እስራት ወይም በሌላ መንገድ ተይዘው ሊሆን ይችላል የሚሉ ወሬዎች ነበሩ፡፡

አንዳንዶች እንዲያውም በሕይወት ስለመኖራቸው ጠይቀዋል።

ከላይ ነው ትዕዛዙ

ሁለት ተከታታይ ክፍሎች ያሉት እና እውነተኛዎቹ የኢንተርኔት ኃያላን 'The Real Internet Giants' በሚል ርዕስ የማ ታሪክ በቢቢሲ ራዲዮ 4 በሥራ ፈጣሪዋ ካትሪን ፓርሰንስ ቀርቧል፡፡

የአሊባባው መስራች የቻይና ባንኮችን "በተለመደው አስተሳሰብ" የሚንቀሳቀሱ ሲሉ ይከሳሉ፡፡ በተጨማሪም ባለሥልጣኖቹ አዲሱን የዲጂታል ፋይናንስ ዓለምን ለመቆጣጠር "የአውሮፕላን ማረፊያውን ለማስተዳደር የባቡር ጣቢያውን አስተዳደር ዘዴ ለመጠቀም እየሞከሩ ነው" ብለዋል። ባንክ ሌላ ዲጂታል ፋይናንስ ሌላ እንደማለት።

መግለጫዎቹ ባንኮቹን አስቆጥቷል። ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግም ሰምተውታል፡፡

ብዙም ሳይቆይ ማ እና የቅርብ የሥራ ባልደረቦቻቸው ከተቆጣጣሪ አካላት ጋር ለመገናኘት ተጠሩ። የአንት ግሩፕ ወደ አክሲዮን ገበያ መግባትም ከግብ ሳይደርስ ቆመ፡፡

የማ ኩባንያዎች የአክሲዮን ዋጋም ወደቀ። ወደ 76 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አጡ፡፡

ከዚያ ስብሰባ በኋላም ጃክ ማ ከዕይታ ተሰወሩ፡፡

'ቀዩን መስመር አለፈ'

"በዚያ ቀን በዢ ጂንፒንግ ቻይና ሊባል እና ሊደረግ ከሚችለው በላይ በመሄድ ቀዩ መስመር አልፏል" ሲሉ ቀደም ሲል ከማ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የቻይና ተንታኝ ክሪስቲና ቡትረፕ ገልጸዋል።

"ለእሱ አስገራሚ ነገር ነው ብዬ አምናለሁ። ምን ያህል መጥፎ ሊሆን እንደሚችል ቢያውቅ ኖሮ ያንን መስመር ባልተሻገረ ነበር፡፡"

ጥር 20 ቀን 2021 ማ በአንድ በጎ አድራጎት ዝግጅት ላይ አጠር ባለች የቪዲዮ መልዕክት እንደገና ታዩ፡፡

በሚቀጥለው ወርም በቻይና ሃይናን ደሴት ጎልፍ ሲጫወት ድጋሚ ታዩ፡፡

"በግልጽ እንደሚታየው በጣም ዝቅ ባለ ሁኔታ ነው የታየው። በእውነቱ ሊያደርገው ከሚችለው በጣም ጥሩው ነገር ነው" ብለዋል ቡትረፕ፡፡

ጃክ ማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰፊው የቴክኖሎጂ ዘርፍ

የቻይና መንግስት ግዙፍ ቴክኖሎጂዎችን የመቆጣጠር አካሄድን እንደገና እያጤነ ነው፡፡ በአሊባባ በበላይነት ገበያው ስለመቆጣጠሩ (ሞኖፖል) ለማጣራት ምርመራ ጀምሯል።

ባለፈው ሳምንት ቴናሴት እና ባይዱን ጨምሮ በ12 ኩባንያዎች 10 ስምምነቶች ላይ የፀረ ሞኖፖል ደንቦችን ይጥሳሉ በማለት ቅጣት አስተላልፏል፡፡ ይህም በሰፊው የቴክኖሎጂ ዘርፍ ውስጥ አለመግባባቶች መባባሳቸውን ሊያመላክት ይችላል፡፡

ቻይና በሆንግ ኮንግ እና በዢንጂያንግ የሰብአዊ መብት ፖሊሲዎቿን በተመለከተ ከአሜሪካ እና ከተቀረው ዓለም ጫና እየደረሰባት ይገኛል፡፡

በቴክኖሎጂ ኃያላን የተወሰደው እርምጃ መረጋጋትን ለማስቀደም እና የንግዱን ስኬት ለመቆጣጠር የተደረገ ጥረት እንደሆነ ይታያል፡፡

"... ፓርቲው እንደ ጃክ ማ ባሉና ተሰሚነት ባላቸው ግለሰቦች ላይ እንኳን ስልጣን እንዳለው ኩባንያዎቹን ለማስታወስ የሚፈልጉ [የኮሚኒስት] ፓርቲ ኮሚቴዎች አሉ" ብለዋል በአውስትራሊያ ስትራቴጂክ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ሳማንታ ሆፍማን፡፡

ይህ ቁጥጥር እስከ ምስጢራዊነት ይደርሳልም ይላሉ፡፡

"ፓርቲው የሚጠይቀውን ለመፈፀም ኃላፊነት ያለበት ኩባንያው ብቻ ሳይሆን ከተጠየቀም ያንን ስለማድረጉ አይስማማም፡፡"

ሌላ ባለሙያ እንደሚጠቁሙት ግን አሊባባ እና ሌሎች ግዙፍ የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በምዕራቡ ዓለም በፖለቲካ መነፅር ብቻ መታየት የለባቸውም፡፡

"ቻይና አሁንም ታዳጊ አገር ነች… በታዳጊ አገር ላይ ካደጉት አገራት ጋር ተመሳሳይ መመዘኛዎችንና ብቃቶችን በመውሰድ መፍረድ አግባብነት የጎደለው ይመስለኛል" ብለዋል የታዋቂው የቻይና የቴክኖሎጂ ዜና መጽሔት ቻይኒዝ ካራክተርስቲክስ ጸሐፊ ሊሊያን ሊ፡፡