ቴክኖሎጂ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ዘልቆ ፊታችንን እያየ ነው

ጭምብ ያደረገች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በፊት ገጽታ የሚከፈት ስልክ የያዙ ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርጎ ስልክ መክፈት እንደማይሞከር ያውቁታል።

ምንም እንኳ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጨርቆች 'ፌሻል ሪኮግኒሽን' [የፊት ቅርፅን አይቶ ማንነት የሚለይ] ቴክኖሎጂን ቢፈታተኑትም አልቻሉትም።

ይህ ጉዳይ ባዕድ ሊመስል ይችላል ግን ቴክኖሎጂ በኮቪድ-19 ምክንያት ፊታችንን ላይ የምናደርገውን መሸፈኛ ዘልቀው እየለየን ነው።

የዓለም ሕዝብ ሳይወድ በግዱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማጥለቅ የጀመረው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ነው።

ይሄኔ ነው የፌሻል ሪኮኒሽን ነቃፊዎች የደስታ ድምጻቸውን ያሰሙት፤ የቴክኖሎጂው ሰዎች ደግሞ በሐዘን አንገታቸውን የደፉት።

የፊትን ገጽታና ቅርጽ አጥንቶ ማንነት የሚለየው ቴክኖሎጂ ማንነትን ለመለየት ሙሉ ፊትን ማየት ይፈልጋል።

አንድ ተቋም 89 ለሕዝብ ጥቅም የሚውሉ ፌሻል ሪኮግኒሽን ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅም ከ5 እስከ 50 በመቶ ስህተት አግኝቶ ነበር።

ጥናቱ የተካሄደው በኮምፒውተር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የተደረገላቸው ፎቶዎችን በመጠቀም ነው።

ነገር ግን አንዳንድ የፊት መለያ ቴክኖሎጂዎች አሁንም መሸፈኛውን ዘልቀው የሰዎችን ማንነት መለየት እየቻሉ ነው።

ባለፈው ጥር የአሜሪካ መንግሥት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት አንድ 96 በመቶ ስኬታማነት ያለው ቴክኖሎጂ አግንኝቷል።

መሥሪያ ቤቱ ባገኘሁት ጥናት መሠረት ፎቶ ተጠቅመው ሰዎች መሸፈኛ ቢያደርጉም ማንነትን መለየት እያቻሉ ነው ብሏል።

የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ሰዎች መሸፈኛቸውን አድርገው ራሳቸውን ከኮቪድ-19 እየጠበቁ ማንነታቸውን መለየቱን እንደክፋት አላየውም።

ማርክ ዛከርበርግ የፌስቡክን ለየት ያለ መነጽር ባስተዋወቀበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማርክ ዛከርበርግ የፌስቡክን ለየት ያለ መነጽር ባስተዋወቀበት

እርግጥ ነው እንደ ለንደን ሜትሮፖለቲን ፖሊስ ያሉ የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች በኮቪድ-19 ምክንያት ቴክኖሎጂውን መጠቀም ቢያቆሙም ባለፈው ዓመት እንደ 'ብላክ ላይቭስ ማተር' ባሉ የጥቁሮች መብት ጠያቂ ሰልፎች ላይ ቴክኖሎጂው እየተሰለለበት ነው።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናሉ ማይክል ክሌይንማን "ቴክኖሎጂው አሁን ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ማለት ወደፊትም ያቆማል ማለት አይደለም" ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

"ማንኛውም ሰው ካሜራ ያለበት አካባቢና የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ግድም ከሄደ ማንነቱ ሊለይ ይችላል" ይላሉ ማይክል።

"ይህ በጣም አስፈሪ ነው። "

የግል መሥሪያ ቤቶች ይህን ቴክኖሎጂ መጠቀም ያቁሙ አያቁሙ በውል አይታወቅም፤ ተመዝግቦ የተቀመጠ መረጃም የለም።

ባለፈው ሰኞ ዲዝኒ ዎርልድ የተሰኘው የመዝናኛ ኩባንያ ይህን ቴክኖሎጂ ለአንድ ወር ያክል ሊሞክረው እንደሚችል ይፋ አድርጓል።

ኩባንያው ደንበኞች ወደ ግቢው ሲገቡ ፊታቸውን በካሜራ ይወስድና ልዩ ቁጥር ይሰጠዋል።

ዲዝኒ ይህን የማደርገው "ደንበኞች ሰልፍ ላይ እንዳይጉላሉ ነው" ይላል።

ታድያ ወደ ዲዝኒ መዝናኛ ፓርክ ሲገቡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎን ማውለቅ አይጠበቅብዎትም።

ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት እንኳ ቴክኖሎጂው ሰዎች ፊታቸውን ሸፍነው እንዴት ማንነታቸውን መለየት ይችላል የሚለውን ሲያጠና ቆይቷል።

ጃፓን ውስጥ አንድ ድርጅቱ በአለርጂ ምክንያት ጭምብል የሚያደርጉ ሰዎችን ማንነት ለመለየት ጥናት ሲያደርግ ነበር።

ድርጅቱ ባለፈው ጥር ጥናቱ 99.9 በመቶ ውጤት ማሳየቱን ይፋ አድርጎ ነበር።

ቴክኖሎጂው ይህን የሚያደርገው በመሸፈኛ ያልተሸፈኑ [ዓይንና ግንባርን የመሳሰሉ] የፊት ክፍሎችን በማጥናት ነው።

ኩባንያው ይህን ቴክኖሎጂ ለትላልቅ ሕንፃዎች ለመሸጥ አስቧል።

ፌሻል ሪኮግኒሽን በሚቀጥለው ሐምሌ በጃፓን በሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተነግሯል።

ቴክኖሎጂው እነማን ላይ እንደሚተገበር ይፋ ባይሆንም ሰዎች ኦሊምፒክ ላይ መጮህና መዝፈን እንደማይፈቀድላቸው ታውጇል።

ፌስቡክም በቅርቡ ይፋ በሚያደርገው 'ስማርት መነጽር ላይ' ይህን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም እንዳሰበ ተናግሯል። ነገር ግን ብዙዎች ይህን ዕቅድ እየተቃወሙት ነው።

ፌሻል ሪኮግኒሽን አሁንም አከራካሪነቱ ቀጥሏል። ወደድንም ጠላንም ቴክኖሎጂው ወደፊት እያደገ መምጣቱ አይቀርም።