ለጃኮብ የተሰራለት ተንቀሳቃሽ ሰው ሰራሽ እጅ ወንድሙን ማቀፍ አስችሎታል

ጃኮብ ከወንድሙ ጋር ተቃቅፎ

የፎቶው ባለመብት, Ben Ryan

የምስሉ መግለጫ, ጃኮብ እጁ ከተገጠመለት በኋላ ወንድሙን በደስታ አቅፎ ታይቷል

ጃኮብ መወለድ ካለበት ሁለት ወራት ቀደም ብሎ ሲወለድ የግራ እጁ አብዛኛው ክፍል በቦታው አልነበረም።

ወላጆቹም ለልጃቸው የሚንቀሳቀስ ሰው ሰራሽ እጅ እንዲሰራለት በኢንተርኔት ላይ 16 ሺህ ፓውንድ ማሰባሰብ ችለዋል።

ብሔራዊው የጤና አገልግሎትና ብዙ ኩባንያዎች የሚሰራ ሰው ሰራሽ እጅ ጃኮብ ባለው ቀሪ የእጅ ክፍል ላይ ብዙም አገልግሎት አይሰጥም ሲሉ ቆይተዋል።

በዚህ ጊዜ ነበር ቤን ሪያን ለአምስት ዓመቱ ጃኮብ ሰው ሰራሽ እጅ ለመስራት ዲዛይን ማድረግ የጀመረው።

ሪያን ቀደም ሲል የአስር ዓመት ልጁ በአደጋ እጁን በመቆረጡ ምክንያት ተንቀሳቃሽ ሰው ሰራሽ አካል አዘጋጅቶ ነበር።

ከዚህም በኋላ ሪያን የሥነ ልቦና መምህርነቱን በመተው 'አምቢዮኒክ' የተባለውን ድርጅትን ካቋቋመ ሁለት ዓመታት አልፈውታል።

ድርጅቱም 'ግሌዝ' ከተባለው የፖላንድ ሰው ሰራሽ አካል አምራች ኩባንያ ጋር በዚህ ዓመት ተዋህዷል።

ሁለቱ ኩባንያዎችን ጥምረት ተከትሎ ምርታቸውን ከተጠቀሙት የመጀመሪያ ተገልጋዮች መካከል ታዳጊው ጃኮብ አንዱ ነው።

ጃኮብ ከእናቱ ከጌማ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Ben Ryan

የምስሉ መግለጫ, ጃኮብ ከእናቱ ከጌማ ጋር

ሪያን ለጃኮብ የተሰራው ተንቀሳቃሽ እጅ የተዋጣለት እንዲሆን የሰው ሰራሽ አካል ባለሙያ ከሆነ ግለሰብና ከጃኮብ ቤተሰቦች ጋር በመሆን ሲሰራ ቆይቷል።

ቤተሰቡ በተለያዩ አቅጣጫዎች መንቀሳቀስ የሚችል፣ ለመጨበጥ የሚያስችልና ከተፈጥሯዊው እጅ ጋር ተቀራራቢ አገልግሎት የሚሰጥ እጅ ልጃቸው እንዲያገኝ ፈልገው ነበር።

ጃኮብና ወንድሙ

የፎቶው ባለመብት, Ben Ryan

የምስሉ መግለጫ, ጃኮብ የሰው ሰራሽ እጁን አድርጎ
ጃኮብ

የፎቶው ባለመብት, Ben Ryan

የምስሉ መግለጫ, ጃኮብ በሚንቀሳቀሰው ሰው ሰራሽ እጁ ነገሮችን መያዝ ይችላል

ለጃኮብ የተሰራው ሰው ሰራሽ እጅ የተለያዩ ተግባራትን አመቺ በሆነ ሁኔታ እንዲከውን የተዘጋጀ ሲሆን ብሪያን ዲዛይኑን አዘጋጅቶ ፖላንድ ውስጥ ያሉት አጋሮቹ ደግሞ እንዳመረቱት ተነግሯል።

ሰው ሰራሹ እጅ ተለቅ ያለና አረንጓዴ ቀለም ያለው ሲሆን "ይህም የጃኮብን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ትልቅ እጅ ሲሆን ከልጁ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ የተሰራ ነው" ሲል ብሪያን ተናግሯል።

ተንቀሳቃሹ ሰው ሰራሽ እጅ ለጃኮብ በተሰጠበት ጊዜ ብሪያን እንዳለው "አሁን ጃኮብ ወንድሙን ማቀፍና እጁን መያዝ ይችላል።"

ጃኮብ

የፎቶው ባለመብት, Ben Ryan

የምስሉ መግለጫ, ጃኮብ ሲወለድ ጀምሮ አብዛኛው የግራ እጅ ክፍል አልነበረውም

ሰው ሰራሹ እጅ ለልጇ ከተገጠመለት በኋላ የፖሊስ መኮንን የሆነችው እናቱ ጌማ ልጇ የተሰራለትን እጅ አድርጎ ማየት "እጅግ ደስ ያሰኛል" በማለት "በጣም ወድጄዋለሁ፤ እሱም አድርጎታል" ስትል ተናግራለች።

እናትየው ጨምራም ጃኮብ የማይንቀሳቀስ ሰው ሰራሽ እጅ እንዲደረግለት ፍላጎት እንዳልነበረው ስትጠቅስ "እንደ ሌሎች ሰዎች እጅ ያለው ሆኖ መታየትን አይፈልግም ነበር" ብላለች።

የተሰራለት ተንቀሳቃሽ ሰው ሰራሽ እጅ ጃኮብ የሰውነት ሚዛኑን እንዲጠብቅ እንደገዘው እናቱ ተናግራለች።

ለጃኮብ ይህንን እጅ ለማሰራት ከተለያዩ ሰዎች የገንዘብ ድጋፍ የተሰበሰበ ሲሆን አንዲት በጎ አድራጊም 5 ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ አበርክታለች። እናቱም የገንዘብ እርዳታ መጠየቅ "ደስ የማይል ስሜትን የሚፈጥር ቢሆንም ማድረግ ያለብንን አድርገናል" ብላለች።

ሰው ሰራሽ እጅ ከላይኛው የእጅ ክፍል የሚጀምር ከሆነ የማይሳካ እንደሆነ ለረጅም ጊዜ ቢታሰብም ብሪያን ዲዛይን ያደረገው የጃኮብ እጅ ግን ይህንን የቆየ እውነታ የለወጠ ነው ተብሏል።

የአምስት ዓመቱ ጃኮብም የተሰራለት ተንቀሳቃሽ እጅ ከሌሎች ተግባራት በተጨማሪ ወንድሙን ለማቀፍ እንዲሁም እጁን ለመያዝ ስለሚያስችለው ተጨማሪ ደስታን ይፈጥርለታል ተብሏል።