ሰው ሰራሽ ልህቀት፡ ሰዎች ከርቀት የሚቆጣጠሯት የሱቅ ሰራተኛ ሮቦት

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, The remote-controlled shop assistant

ዓለም በቴክኖሎጂ እየተራቀቀ ነው። በተለይ የሰው ሰራሽ ልህቀት [አርተፊሻል ኢንተለጀንስ] ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።

አሁን ላይ ሰዎችን ተክተው የሚሰሩ ሮቦቶችን ማየቱ አዲስ አይደለም።

በጃፓኗ መዲና ቶክዮ በሚገኝ አንድ አነስተኛ የገበያ ማዕከልም አንዲት ሮቦት ሥራዋን በትጋት እየተወጣች ነው።

ሰዎች የሚፈልጓቸውን የመጠጥ አይነቶች ታነሳለች፤ ትሰጣለች፤ በማቀዝቀዣው መደርደሪያ ላይ ታስቀምጣለች። ብቻ ብቻዋን ተፍ ተፍ ትላለች። ሰዎችም ይመጣሉ፤ ይሄዳሉ።

የሮቦቷ ሥሪት በጣም የተቀናጀና ራስ ገዝ የመካኒካል ሥራ ይመስላል፤ ግን አይደለም። ሮቦቷ የራሷ አዕምሮ የላትም። እንደ ሰው አታስብም። ሥራዋን የምትወጣው ከብዙ ኪሎ ርቀት ላይ ሆኖ በሚቆጣጠራት ሰው አማካይነት ነው።

የሮቦቷን እይታ በሚሰጠው 'በቨርቹዋል ሪያሊቲ' [ምናባዊ እውነታ] መመልከቻ መሳሪያ ማለት ነው።

ሮቦቷ የጃፓኑ ቴልኤግዚስታንስ ድርጅት ሥራ ውጤት ናት። 'ሞዴል ቲ' የተሰኘው የሮቦት ዲዛይኑ ሰዎች ከቤታቸው ወይም ከሌላ ሩቅ ቦታ ሆነው የሰዎችን ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎችን እንዲሰሩ የሚያስችል ነው።

የድርጅቱ የቦርድ ዳሬክተር ዩቺሮ ሂኮሳካ የሮቦት ሞዴሉ "አምሳለ ሰው" ነው ብለዋል።

"ባላችሁበት ሆናችሁ የፈለጋችሁበት ቦታ መሄድ ትችላላችሁ" ብለዋል ዳሬክተሩ፤

የቴክኖሎጂ ሥራው ቴሌሮቦቲክስ ወይም በስልክ የሚሰራ ሮቦት ይባላል። ይህም በሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልሞች በሆኑት ሰሮጌትስ እና ሰሊፕ ዲለር ፊልሞች ላይ ተስለው ታይተዋል።

በርቀት በመቆጣጠር ቦምብ የሚጥሉ ሮቦቶች ለዘመናት ያሉ ሲሆን ፤ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ምግብ ለሰዎች ቤት የሚያደርሱ ሮቦቶችን ጨምሮ በቴሌ የሚሰሩ መሳሪያዎች ቀድሞ ከነበረው በይበልጥ እየተሰሩ ነው።

ዳሬክተሩ "በእድሜ የገፉ በርካታ ሕዝብ የሚኖርባት ጃፓን፤ አሁን ላይ የሰው ኃይል እጥረት አለባት። በተለይ ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ ችግሩ ይብሳል" በማለት የፈጠራ ስራው ይህን ሊያቃልል እንደሚችል ተናግረዋል።

አካላዊ መገኘትን በሚጠይቁ ሥራዎች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮቦቶችን በማሰማራት በተወሰነ መልኩ ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻልም አክለዋል። ይህ ድርጅቶች በርቀት የሚቆጣጠሩ ሰራተኞችን ለመቅጠር ያስችላቸዋል በማለትም ጠቀሜታውን አስረድተዋል።

"መጀመሪያ ቶክዮ ሰርቶ ከአስር ደቂቃ በኋላ ደግሞ ሆካይዶ መስራት ይቻላል" ብለዋል። በመኪና አሊያም በባቡር መጓዝ ሳጠበቅብዎት ማለት ነው።

ሮቦቶቹን የሚቆጣጠሩት ሰራተኞች በኦንላይን መገበያያ ቦታው በመግባት፣ መስራት የሚፈልጉትን በመምረጥ እና 'ቨርቹዋል ሪያሊቲ' ማዳመጫውን በማድረግ ሮቦቶችን እንዲሰሩ ማንቀሳቀስ ይችላሉ።

ቴልኤግሲስታንስ ሮቦት

የፎቶው ባለመብት, Telexistence

የምስሉ መግለጫ, አንድ ሰው በተለያዩ ቦታዎች ያሉ በርካታ ሮቦቶችን መቆጣጠር ይችላል

"ሃሳቡ በተለይ አሁን ባለንበት ወቅት ተስፋ ሰጭ ነው። ምክንያቱም ሰዎች ከሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ስለሚቀንስ ለወረርሽኙ የመጋለጥ እድላቸውን ይቀንሳል" ብለዋል ዳሬክተሩ።

ይሁን እንጅ ድርጅቱ ያልፈታቸው ችግሮች መኖራቸውንም ሳይገልፁ አላለፉም።

'ሞዴል ቲ' ሮቦቶች የሰው ያህል በፍጥነት መንቀሳቀስ አይችሉም፤ እንዲሁም የሚቆጣጠረው ሰው የሚያደርው 'ቨርቹዋል ሪያሊቲ' [ ምናባዊ እውነታ] መከታተያውን በተለይ ደግሞ ለረዥም ጊዜ ካደረገውየመፍዘዝና የማጥወልወል ስሜት ሊፈጥር ይችላል።

በመሆኑም እርሳቸውና ባልደረቦቻቸው ለዚህ ችግር መፍትሔ ለማፈላለግ እየሰሩ መሆናቸውን ዳሬክተሩ ተናግረዋል።