ባለፉት ሁለት ሳምንት ፓርኮችንና ጥብቅ ደኖችን እያወደመ ያለው እሳት

የፎቶው ባለመብት, Ankober communication
በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ከባድ ጉዳትን ያደረሱ የእሳት አደጋዎች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ቆይተዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ የገበያ ስፍራዎችና የመኖሪያ አካባቢዎች ላይ በተከታታይ በደረሱ የእሳት አደጋዎች በሚሊዮኖች ብር የሚገመት ንብረት ለውድመት መዳረጉ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ ባለንበት የመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮችና ጥብቅ ደኖች ላይ የእሳት አደጋ አጋጥሞ ከባድ ውድመትን አድርሷል።
በእነዚህ የተፈጥሮ ደኖች ላይ ያጋጠመውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ሲሆን በስሜን ብሔራዊ ፓርክ ላይ የደረሰው ቃጠሎ መጥፋቱ የተነገረ ቢሆንም በሌሎቹ አካባቢዎች ግን እሳቱ ለቀናት ቀጥሏል።

መጋቢት 2/2013፡ በሃላይደጌ አሰቦት ዕጩ ብሔራዊ ፓርክ ሰሜናዊ ክፍል የተከሰተው የእሳት አደጋ በተከሰተ የእሳት አደጋ እስካሁን ከ100 ኪሎ ሜትር ስኩየር በላይ የሚገመት ሳርና ቁጥቋጦ መውደሙ ተገልጿል።
በደረቅ የአየር ሁኔታና በአካባቢው ባለው ከፍተኛ ንፋስና ምክንያት ቃጠሎው በፍጥነት እየተስፋፋ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሆነ ተነግሯል።
መጋቢት 5/2013፡ የአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካል በሆነው የጭላሎ ጋለማ ደን ላይ የእሳት አደጋ ተከስቶ ረጅም እድሜ ያላቸው የዛፍ አይነቶች ላይ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል።
ለቀናት የቆየው የእሳት አደጋው ሰፊ ቦታን የሸፈነ ሲሆን ፓርኩ ከሚያካትታቸው ዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ በሰባቱ የእሳት አደጋው ውድምትን አድርሷል።
የእሳቱ መንስኤ ለግጦሽና የዱር እንስሳትን ለመከላከል በሚል በተለኮሰ እሳት ሳቢያ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የጭላሎ ተራራ በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ የእሳት አደጋዎች አጋጥሞታል።
መጋቢት 12/2013፡ በግዙፉ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የእሳት ቃጠሎ ተከስቶ ከባድ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነግሯል።
ምክንያቱ ያልታወቀው በፓርኩ ገደላማ አካባቢዎች የተነሳው ይህ የእሳት አደጋ በሳርና በአንዳንድ ዛፎች ላይ የተወሰነ ጉዳት አድርሶ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን በፓርኩ ውስጥ በሚገኙ የዱር እንሰሳት ላይ ጉዳት አለመድረሱ ተነግሯል።
ከዚህ ቀደምም የፓርኩን ሰፊ ቦታ ያዳረሰና ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብት ውድመትን ያስከተለ የእሳት አደጋ ተከስቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።
መጋቢት 13/2013፡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኘው ወፍ ዋሻ በተባለው ደን ላይ የእሳት ቃጠሎ ተከስቶ በፍጥነት መስፋፋቱ ተነግሯል።
እሳቱ በአንኮበር ወረዳ በኩል በሚገኘው የደኑ ክፍል ላይ ተነስቶ ሦስት ቀበሌዎችን ላይ በሚገኝ ደን ላይ ውድመትን አድርሷል።
ከባድ ጉዳትን ያደረሰው ይህ የእሳት ቃጠሎ ከግለሰብ ማሳ የተነሳ እሳት ወደ ደኑ በመዛመቱ መሆኑ ተገልጿል።
መጋቢት 14/2013፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኘውና ጅባት ተብሎ የሚታወቀው ደን ላይ ካለፈው ማክሰኞ የጀመረ የአሳት ቃጠሎ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ነዋሪዎችና ባለስልጣናት የተናገሩ ሲሆን፤ አደጋው እስካሁን 1 ሺህ ሄክታር የሚሸፍን ደን ማውደሙን ተገልጿል።
የእሳቱ ምክንያት ምን እንደሆነ በትክክል የታወቀ ነገር ባይኖርም አደጋው ግን እጅግ የከፋ በመሆኑ በአካባቢው ነዋሪ ጥረት ብቻ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሆነ ተነገሯል።
የጅባት ጥብቅ ደን 27 ሺህ ሄክታር መሬትን የሚሸፍን ሲሆን በውስጡም በርካታ የአእዋፋት ዝርያና የተለያዩ የዱር እንስሳት መኖሪያ ነው።

የፎቶው ባለመብት, FB

የእሳቱ መንስኤ ምንድን ነው?
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰለሞን መኮንን እንደሚሉት፤ እነዚህ ስፍራዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ደን ያለባቸውና በረሃማ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ሰደድ እሣት በራሱ ጊዜ የሚነሳበት ወቅት አለ።
ሌላኛው ደግሞ ሰዎች በጫካዎቹ ውስጥ ያለውን ማር ለመቁረጥ ወይም ከሰል ለማክሰል ሲሉ የሚለኩሱት እሳት ከቁጥጥር ውጪ በመሆን ወደ ፓርኮቹ በመዛመት ከባድ ውድመትን ሊያስከትሉ ይችላል ብለዋል።
በተጨማሪም አብዛኞቹ ፓርኮች የግጦሽ መሬት ስላላቸው አሁን ወቅቱ በጋ በመሆኑ ለከብቶቻቸው የማይሆነውን የደረቀ ሳር እዚያው መስክ ላይ እንዳለ በማቃጠል አዲስ ሳር እንዲበቅል ለማድረግ በሚል በሚለኮስ እሳት ውድመት ሊከሰት ይችላል ሲሉ አቶ ሰለሞን ምክንያቶቹን አስቀምጠዋል።
ስለዚህ በደኖች ውስጥ ካለው በጣም ደረቅ የአየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ እሳት የሚነሳበት ሁኔታ እንዳለው ሁሉ በሰዎች አማካይነት የሚፈጠሩ የእሳት አደጋዎች ስላሉ "መነሻዎቹ ተፈጥራዊና ሰው ሠራሽ ናቸው" ይላሉ።
















