ከሰሞኑ የተከሰቱ ሰደድ እሣቶች ምክንያት ተፈጥሯዊ ወይስ ሰው ሰራሽ?

የፎቶው ባለመብት, Taajuu Abdii
ከሰሞኑ በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርኮችና ደኖች ላይ እሣት እየተነሳ ጥፋት እያደረሰ እንደሆነ ሲዘገብ ቆይቷል። ለመሆኑ የእነዚህ የእሣት ክስተቶች ምክንያት ምንድነው? ሰው ሰራሽ ወይስ ተፈጥሯዊ?
አቶ ሰለሞን መኮንን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ እንደሚሉት በተወሰኑ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ እሣት በተደጋጋሚ ይነሳል።
ከዚህ አንጻር በተለይ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዋናነት፤ አልፎ አልፎ ደግሞ በነጭ ሣርና ሐላይደጌ-አሰቦት ብሔራዊ ፓርኮችም በተለያዩ ጊዜያት እሣት እየተከሰተ በደን፣ በእጸዋትና በእንስሳት ላይ ጉዳት ይደርሳል።
"እነዚህ ቦታዎች ከፍተኛ ደን ያለባቸውና በረሃማ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ሰደድ እሣት በራሱ ጊዜ የሚነሳበት ወቅት አለ። ሌላኛው ደግሞ ሰዎች ማር ለመቁረጥ አሊያም ከሰል ለማክሰል የሚለኩሱት እሳት ወደ ፓርኩ ይዛመታል" ይላሉ አቶ ሰለሞን ከምክንያቶቹ መካከል ሲጠቅሱ።
ጨምረውም አብዛኞቹ ፓርኮች የግጦሽ መሬት ስላላቸው ወቅቱ በጋ መሆኑን ተከትሎ የደረቁ ሳሮችን አቃጥሎ ሌላ እንዲበቅል በሚል እሣት ስለሚለኮስ ከቁጥጥር እየወጣ ጉዳትን ያደርሳል።
"ስለዚህ መነሻዎቹ ተፈጥራዊና ሰው ሠራሽ ናቸው" በማለት የሚነሱትን የደን ቃጠሎዎች ምክንያት አስቀምጠዋል።
በቅርቡ በአሰቦት የተከሰተው እሣት መነሻው ምንድን ነው ተብሎው የተጠየቁት ኃላፊው "መነሻውን እያጠናን ነው። አንዳንድ ፍንጮች እዚያ አካባቢ የቦታ ውዝግብ ስለነበር ከዚያ ጋር ተያይዞ የተነሳ እንደሆነ ጠቁመውናል። ነገር ግን ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር ይሄ ነው ወይ አይደለም የሚለውን ነገር አጥንተን ትክክለኛውን መረጃ ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው" ይላሉ።
"እዚያ አካባቢ ያለውን ማሕበረሰብ አስተባብረን እሣቱን የማጥፋት ሥራ ከሠራን በኋላ ማነው የፈጠረው፣ በምንድን ነው የተፈጠረው የሚለው በሁለተኛ ደረጃ የሚመጣ ነው። ነገር ግን ለሰደድ እሣቱ ተጨማሪ ምክንያት ይኖራል ብለን እንገምታለን" ብለዋል።
ኃላፊው ሰዎች ሆን ብለው አድርገውት ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ አለን በማለት፣ "በእርግጠኝነት ነው አይደለም የሚለው ግን ማጣራት ይሻል" ባይ ናቸው።
"በዚህ ዓመት ብቻ አሰቦት ፓርክ ላይ ሶስት ጊዜ እሣት አደጋ ደርሷል። ሁለቱን ብዙ አደጋ ሳያደርሱ ለመቆጣጠር ችለናል። አንደኛው ግን ጉዳት አድርሷል ቅድም እንደገለፅኩት። የጉዳት መጠኑን የሚመረምር ኮሚቴ ለማቋቋም ጥረት እያደረግን ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Taajuu Abdii
አሰቦት ላይ ከዚህ በፊት የተነሱት ሰደድ እሣቶች ግን ከከሰልና ማር ቆረጣ ጋር የሚገናኝ እንጂ ሆን ተብሎ እንዳልሆነ አቶ ሰለሞን ይገልፃሉ።
በሌላ በኩል በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከሰሞኑ እሣት ተነስቶ ብዙ ጉዳት ሳያደርስ ወዲያው ለመቆጣጠር ተችሏል ይላሉ።
የሰደድ እሣቱን ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከዩኔስኮ ባገኘው ድጋፍ አማካይነት የእሣት ብርጌድ እንደተቋቋመና ይህ ሥልጠናም የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ተራራ ላይ የተነሳውን እሣት ለመቆጣጠር እንደጠቀመ ይናገራሉ።
ኃላፊው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ቅድመ ዝግጅት ማድረግና አደጋው ሲከሰት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንደሚያሻ ገልፀዋል።
"አሁን ሃገራትን ስናይ እንደዚህ ዓይነት ችግር ሲያጋጥም የሚጠቀሙበት ሄሊኮፕተር አላቸው። ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካን መጥቀስ ይቻላል። በዚህ ደረጃ ራሳቸውን ገንበተው ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት። እኛም በዚህ ደረጃ መንቀሳቀስ አለብን። በሂደት እንደዚህ ዓይነት አቅም ይኖረናል የሚል እምነት አለኝ።"
አሁን ባለው ሁኔታ ሰው ሰራሽ የእሣት ምክንያቶችን ለመግታት ትልቁ ግንዛቤ መፍጠር ነው ይላሉ ኃላፊው።
"ሕብረተሰቡ ይህ ፓርክ የኔ ነው የሚል የባለቤትነት መንፈስ መፍጠር አለብን። በርካታ የንቅናቄ መድረኮችን እየፈጠርን እንገኛለን። አቅም ከመገንባት አንፃር ግን የሆነ ችግር ቢፈጠር በፍጥነት ደርሰን በቴክኖሎጂ ታግዘን የምንፈታበት ደረጃ ላይ አይደለንም።"
አሰቦት ላይ የደረሰው አደጋ በቴክኖሎጂ የታገዘ ምላሽ ቢሰጥ ይህ ሁሉ ጥፋት አይደርስም ነበር ይላሉ።
ኃላፊው መሥሪያ ቤታቸው አቅሙን ለማጠናከር ይረዳው ዘንድ እገዛ እንዲደረግለት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ድረስ ጥያቄ ማቅረቡን ይናገራሉ።
"ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተፈጥሮ ሃብት ካላቸው ተነሳሽነት አንፃር ጥያቄያችን ምላሽ ያገኛል የሚል እምነት አለን። ምላሽ እየተጠባበቅን ነው የምንገኘው" ሲሉም አክለዋል።
ባለፈው ዓመት በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሄሊኮፕተር ለመግዛት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።
ግዢው ከምን ደረሰ ተብለው የተጠየቁት አቶ ሰለሞን "በወቅቱ በዩኔስኮ እገዛ ሄሊኮፕተር መጥቶ እሣቱ ሊጠፋ እንደቻለ ይታወሳል። ከዚያ በኋላ ችግሩን ለመፍታት ሄሊኮፕተር እንደሚገዛ ተነግሮ ነበር ነገር ግን እስካሁን በተግባር ያየነው ነገር የለም" ብለዋል።
ከሰሞኑ የተነሱት ሰደድ እሣቶች በዱር እንስሳትና በደን ላይ ያደረሰውን ጉዳት መጠን ለመረዳት ጥናት እንደሚያሻም ይናገራሉ።
ባለፈው ዓመት ግን በተለያዩ ብሔራዊ ፓርኮች የደረሱት ጉዳቶች ሰፊ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፣ የዱር እንስሳት ሰደድ እሣት በሚነሳ ወቅት ስለሚሸሹ የደረሰባቸውን ጉዳት የሚያሳይ ጥናት የለም ይላሉ።














