አልጀሪያውያኑ ለሳምንታት ኑሯቸውን በፓሪስ አየር ማረፊያ አድርገዋል ተባለ

አልጀሪያውያን መንገደኞች

ከዩናይትድ ኪንግደም መነሻቸውን ያደረጉ ሃያ ስድስት አልጀሪያውያን ከፓሪስ አየር ማረፊያ መውጣት አልቻሉም ተብሏል።

በፖሪሱ ቻርለስ ደ ጎል አየር ማረፊያም ውስጥ ለሶስት ሳምንታት ያህል መኖሪያቸውን አድርገዋል ተብሏል።

ከእንግሊዝ የተነሱት እነዚህ አልጀሪያውያን ውስጥ ሁለት ህፃናትና አንዲት የ75 አዛውንት አሉበት ተብሏል።

መንገደኞቹ ፓሪስ ሲደርሱ አሳፍሯቸው የነበረው የአልጀሪያ አየር መንገድ ኤይር አልጀሪያ በኮቪድ-19 መመሪያዎች ምክንያት ጉዟቸውን መቀጠል እንደማይችሉ ተነገራቸው።

ከዚያም በኋላ አለም አቀፍ መንገደኞች መሻገሪያ በሆነው ተርሚናል 2 ውስጥ መኖሪያቸውን አድርገዋል ተብሏል።

በፓሪስ ተቀማጭነቱን ያደረገው የአልጀሪያ ኤምባሲ ለቢቢሲ እንደተናገረው ከበረራቸው በፊት ቲኬታቸውን መሰረዙን ለመንገደኞች አስታውቋል።

በአልጄሪያ ውስጥ የዩኬ-ኬንት ኮቪድ ዝርያ መገኘቱንም ተከትሎ ነው መንገደኞቹ እንዳይገቡ የተደረገው።

ከመንገደኞቹ መካከል አንደኛው እንደተናገረው አንዳንዶቹ የእንግሊዝ ፓስፖርት ያላቸው ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ በእንግሊዝ ነዋሪነታቸውን ያደረጉ ወይም የእንግሊዝ ቪዛ ያላቸው ናቸው።

የአንዲት ሴት ቪዛም ጊዜው አልፎበታል ተብሏል። ሌላኛው ደግሞ "ህገ ወጥ ስደተኛ' ነህ በሚል ወደ አልጀሪያ የሚመለስ መንገደኛ ነው ተብሏል።

ሁሉም መንገደኞች ቢሆን ወደ አልጀሪያ የሚመለሱበት አፋጣኝ ምክንያት እንዳላቸው ነው።

አንዳንዶቹም የታመመዙ ዘመዶች አሏቸው ተብሏል።

አየር ማረፊያው ላይ ከደረሱ በወለሎች ላይ እንዲሁም በወንበሮች ላይ እየተኙ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ምግብ የሚያገኙት ከበጎ ፈቃደኞች ነው ተብሏል። ሌላኛው መንገደኛ በሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገለት መሆኑ ተነግሯል።

የመንግሥት ንብረት የሆነው ኤይር አልጀሪያ መጀመሪያ አካባቢ ለመንገደኞቹ ነፃ ምግብ እየሰጠ የነበረ ቢሆንም ወደ ለንደን ልመልሳችሁ ሲል እምቢ በማለታቸው ምግብ መስጠቱን አቁሟል ተብሏል።