ባይደን በፑቲን ላይ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ ሩሲያ አምባሳደሯን ጠራች

የሩሲያ አምባሳሰደር አናቶሊ አንቶኖቭ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩሲያ ዋሽንግተን የሚገኙ አምባሳደሯን ለውይይት በሚል ከሰሞኑ ጠርታለች።

ከአሜሪካ ጋር ያለው የሻከረ ግንኙነት የማይቀለበስ ደረጃ ላይ እንዳይደርስም ለመምከር ነው ተብሏል።

የሩሲያ መንግሥት እንዳሳወቀው አምባሳደር አናቶሊ አንቶኖቭ ወደ ሞስኮ የተጠሩበት ምክንያት አገሪቷ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት መጥፎ ሁኔታ ላይ በመድረሱ ያንን አቅጣጫ ለማስያዝ ነው ብሏል።

ይህንን ውሳኔ ሩሲያ ያሳወቀችው ፕሬዚዳንት ባይደን በአሜሪካ ምርጫ ላይ ጣልቃ ገብተዋል የሚባሉትን ቭላድሚር ፑቲንን "ዋጋ ይከፍላሉ" ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

ከቅርብ ወራት በፊት የአሜሪካ መንበረ ስልጣንን የተቆጣጠሩት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከኤቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፕሬዚዳንት ፑቲን "ነፍሰ ገዳይ ናቸው" ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል።

በጥቅምት ወር መጨረሻ በተደረገው የአሜሪካ ምርጫ ላይ ጣልቃ የመግባት ዘመቻን ፕሬዚዳንት ፑቲን መፍቀዳቸውን አንድ የአሜሪካ ደህንነት ሪፖርት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው ባይደን ይህንን የተናገሩት።

ሪፖርቱ ሩሲያ ተሰናባቹን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሸናፊ እንዲሆኑ ጣልቃ በመግባት አስተዋፅኦ አድርጋለች በማለት ወንጅሏታል።

ሩሲያ ጣልቃ በመግባቷ ምን አይነት ውጤቶች ሊኖሩ ይችላሉ ተብለው የተጠየቁት ፕሬዚዳንት ባይደን"በቅርቡ ታዩታላችሁ" ብለዋል።

የፕሬዚዳንት ፑቲን ቃለ አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው ውንጀላው በመረጃ ያልታገዘና የሁለትዮሽ ግንኙነቱንም በቀጣዩ የሚጎዳ ነው ብለውታል።

የሪፖርቱ ማጠቃለያን ተከትሎ አሜሪካ በሚቀጥለው ሳምንት በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ትጥላለች ተብሎ ይጠበቃል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ምን አለ?

"በአሜሪካ የሚገኙት የሩሲያ አምባሳደር አናቶሊ አንቶኖቭ ወደ ሞስኮ የተጠሩት ለምክክር ነው። የሁለቱን አገራት ግንኙነት በተመለከተ አውዱ ምን ሊሆን ይገባል የሚለው ላይ ትንታኔም ይሰጣል" በማለት መግለጫው አትቷል።

ሩሲያ አክላም በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መሻከር የማይቀለበስ ደረጃ ከመድረሱ በፊትም መካላከል እንደምትፈልግ አስታውቃለች።