በአትላንታ ስድስት እስያውያን ሴቶች የሞቱበትን ጥቃት የፈፀመው ግለሰብ በግድያ ወንጀል ተከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአትላንታ፣ ጆርጂያ ግዛት በሚገኙ ስፓዎች ተኩስ ከፍቶ ስምንት ሰዎችን የገደለው ግለሰብ በግድያ ወንጀል መከሰሱ ተሰምቷል
ፖሊስ የተጠቂዎችን ማንነትም እያጣራ ቢሆንም ስድስቱ እስያውያን ናቸው ተብሏል።
በዚህ ግድያ ስድስት እስያውያን ሴቶች ቢሞቱም ፖሊስ ዘር ላይ ያነጣጠረ ስለመሆኑ ገና አላረጋገጥኩም ብሏል።
አራቱ ሰለባዎች በትናንትናው ዕለት ስማቸው ይፋ ተደርጓል።
ተጠርጣሪው በበርካታ የግድያ ወንጀሎችም ክስ እስር ሊጠብቀው ይችላል ተብሏል።
ግድያውን የፈፀመው ሮበርት አሮን ሎንግ የሚባል የ21 ዓመት ግለሰብ ነው።
የቼሪሮኬ ካውንቲ ሸሪፍ ፍራንክ ሬይኖልድስ እንዳሳወቁት ግለሰቡ የ"ወሲብ ሱሰኛ ነኝ" ማለቱን ነው።
ከዚህ ቀደም እስያውያን ላይ የጥላቻ ወንጀሎች ቢኖሩም በቅርቡ ደግሞ የሚደርሱ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅበዋል ተብሏል።
አራቱ ሰለባዎች አሽሊ ያውን 33፣ ፓውል አንድሬ ሚሸልስ54፣ ኪሳዎጄ ታን 49ና ዳዩ ፌንግ 44 ናቸው። ኤሊካስ አር ሄርናንዴዝ ኦርቲዝ በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባት መካከል ናት ተብሏል።
ንዴትና ፍራቻ በእስያውያን ማህበረሰብ
ልባችን ተሰብሯል፣ ፈርተናል እንዲሁም ተሰላችተናል የሚሉ ቃላቶችን ነበር በአሜሪካ የሚኖሩ እስያውያን ከግድያው በኋላ የተናገሩት። በርካቶች ከተኩሱ በኋላ በዋሽንግተን ዲሲ ሻማ በማብራት በሞት የተለዩዋቸውን ዘክረዋል።
ቻይናታውን ተብሎ በሚጠራው ሰፈርም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአትላንታ ግድያ ለተነጠቁት ስምንት ሰዎች ሃዘናቸውን ሻማ በማብራት ገልፀዋል።
ባለስልጣናቱ ግድያዎቹን ከፀረ-እስያውያን የጥላቻ ወንጀል ጋር ባያገናኙትም በርካቶች ግን በእስያውያን ላይ ያነጣጠረ ወንጀል እንደሆነ እየተናገሩ ነው።
"በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካ እስያዊ ዝርያ ያላት ሴት መሆን አስፈሪ ነው" ነው በማለት አንዲት እስያዊ አሜሪካዊ ሴት ለቢቢሲ ተናግራለች።
ስታድግ ከፍተኛ የሆነ ዘረኝነት ተጠቂ ብትሆንም ቤተሰቦቿ ዝምታን እንድትመርጥ በማድረጋቸው ለአመታት በዝምታ ተሸብባ እንደነበርም አስረድታለች።
ስለ ተኩስሱምን እናውቃለን?
የመጀመሪያው የተኩስ ልውውጥ የተከናወነው በቼሮኪ አውራጃ በአክዎርዝ በሚገኘው በያንግ ኤሲያን ማሳጅ ፓርለር ነበር፡፡
የፖሊስ ቃል አቀባዩ ካፕቴይን ጄይ ቤከር ሁለት ሰዎች በቦታው መሞታቸውንና ሶስት ሰዎች ደግሞ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ገልፀዋል።
ሆስፒታል ውስጥ ሌሎች ሁለት ሰዎች እንደሞቱ ተናግረዋል፡፡ ከተጎጂዎቹ ሁለቱ የእስያ ዝርያ ያለባቸው ወንድ እና ሴት መሆናቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ሌላ የሂስፓኒክ ዝርያ ያለበት ግለሰብ መቁሰሉን ተናግረዋል።
ከአንድ ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በሰሜን ምስራቅ አትላንታ በሚገኘው ጎልድ ስፓ "ዝርፊያ እየተካሄደ ነው" በሚል ፖሊስ መጠራቱን ገልጿል።
ፖሊስ በሪፖርቱ እንደገለጸው "ፖሊሶች በቦታው በደረሱበት ወቅት የሞቱ ሶስት ሴቶች ተገኝተዋል፡፡
ከመንገዱ ባሸገር በሚገኘው የአሮማቴራፒ ስፓ የተጠሩት ፖሊሶች የተገደለች ሌላ ሴት አግኝተዋል፡፡
የአትላንታ ጆርናል-ኮንስቲትዩሽን፣ ፖሊስን ጠቅሶ እንዳስታወቀው ስድስቱ የአትላንታ ተጠቂዎች የእስያ ዝርያ ያላቸው ሴቶች ናቸው፡፡
መርማሪዎች በአንዱ ስፓ አቅራቢያ የተቀረጸን የተጠርጣሪ ምስል ለቅቀዋል፡፡
በጆርጂያ ጆርጅ ዉድስቶክ ነዋሪ የሆነው ሮበርት አሮን ሎንግ ከአትላንታ በስተደቡብ 240 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ክሪስፕ ካውንቲ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታውቋል፡፡












