በርካታ ኢትዮጵያውያን በሞቱብት ቃጠሎ 'ጥልቅ ሃዘን' እንደተሰማው የየመኑ ሁቲ አማፂ ገለፀ

በሰንዓ የአፍሪካ ማህበረሰብ ተወካዮች

የፎቶው ባለመብት, EPA

በየመን መዲና ሰንዓ በሚገኝ አንድ የስደተኞች እስር ቤት ውስጥ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ለጠፋው ህይወት ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማው የየመኒ አማፂ ቡድን አስታውቋል።

የ44 ስደተኞችን ህይወት የቀጠፈው እንዲሁም 193 ደግሞ የተጎዱበትን የእሳት ቃጠሎ ድንገተኛ መሆኑንም ከፍተኛ የሁቱ ባለስልጣን አስታውቀዋል።

"በሰንዓ የስደተኞች እስር ቤት የተነሳው ድንገተኛ እሳት አደጋ የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን ማስተላለፍ እንፈልጋለን" በማለት የሁቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁሴን አል አዚ በአማፂው በሚቆጣጠረው አል ማሲራህ ቴሌቪዥን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

"አደጋው እንዴት እንደተነሳ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነም ጠቅሰዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነፃ የሆነ ምርመራ እንዲደረግ አጥብቆ ጠይቋል።

ሂውማን ራይት ዋች በበኩሉ ማዕከሉ ላይ የተተኮሰ መሳሪያ ለቃጠሎው መነሻ እንደሆነ ጠቅሶ ለዚህም የሁቱ አማፂያንን ጥፋተኛ አድርጓቸዋል።

ሁሴን አል አዚ የእሳት ቃጠሎውን አስመልክቶ ሃዘናቸውን የገለፁና ያደረሰውንም ጥፋት የገለፁ የመጀመሪያ ባለስልጣን ቢሆኑም የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርትን በተመለከተ በዝምታ አልፈውታል።

የአይን እማኞች እንደተናገሩት በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ የሆኑበት በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በእስር ቤቱ በተፋፈገና ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ሁኔታ እየተቃወሙ ባለበት ወቅት የፀጥታ ኃይሎችና ጥበቃዎች ሊያስቆማቸው እንደሞከሩ ነው።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችንም ሰብስበዋቸው ባሉበት ወቅት አንድ የፀጥታ ኃይል የማዕከሉ ጣሪያ ላይ ወጥቶ መሳሪያ እንደተኮሰ ነው።

የመጀመሪያው ተኩስ ጭስና እንባ ብቻ ቢያስከትልም ሁለተኛው ግን በከፍተኛ ሁኔታ ፈንድቶ የእሳት ቃጠሎ ማስነሳቱን ተናግረዋል።

ሂውማን ራይትስ ዋች ምን አይነት መሳሪያ እንደተጠቀሙ ያለው ነገር ባይኖርም የጭስ ቦምብ፣ እንዲሁ ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

"በጣም ነው የደነገጥኩት፤ ጭንቅላቴ በጭሱ የተደፈነ ነው የመሰለኝ። ሰዎች እየሳሉ ነበር። ፍራሹና ብርድ ልብሱ በእሳት ተቀጣጠለ" በማለት አንድ የ20 አመት ስደተኛ ተናግሯል።

"ሰዎች በህይወት እየተቃጠሉ ነበር። ከሚቃጠሉ አስከሬኖች ራሴን ገለል ማድረግ ነበረብኝ" ብሏል።

ሂውማን ራይትስ ዋች እንዳስታወቀው በርካታ የፀጥታ ኃይሎች ሆስፒታሎችን ከበው እንደነበርና ቀለል ያለ ጉዳት የደረሰባቸውን እስረኞችንም መልሰው እንዳሰሯቸው ተገልጿል።

"የሁቱ ባለስልጣናት ስደተኞቹን እንዲህ ባለ አሰቃቂ ሁኔታና ህይወታቸውን አደጋ ውስጥ በሚከት ሁኔታ መያዝ መቆም አለባቸው። ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል" በማለት የሂውማን ራይትስ ዋች የስደተኞችና ተፈናቃዮች መብት ተመራማሪ አሳውቀዋል።

ሁቱዊች ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ዋና መዲናዋን ሰንዓን ጨምሮ የሰሜን ምዕራብ ግዛቶችን ተቆጣጥሯል።