በታይዋን ሬስቶራንት በነፃ ለመመገብ ሲሉ በርካቶች ስማቸውን መቀየራቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከሰሞኑ የታይዋን ዜጎች ስማቸውን "ሳልመን" ወደሚባል የአሳ ዝርያ ቀይረዋል ተባለ።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አንድ ሬስቶራንት 'ሳልመን' የሚል ስም ያላቸው ሰዎች በነፃ ሱሺ መመገብ ይችላሉ በማለት ያወጣውን ማስታወቂያ ተከትሎ ነው።
በርካቶችም ስማቸውን ለማስቀየር የሚመለከታቸው የመንግሥት መስሪያ ቤቶች መሄዳቸውን ተከትሎ ባለስልጣናቱ "እባካችሁ ስማችሁን መቀየር አቁሙ" በማለት መማፀናቸውን የአገሪቱ ሚዲያ ግቧል።
ሬስቶራንቱ "ጁይ ዩ ወይም ሳልመን የሚል ስም ያላችሁ ሰዎች በነፃ ለመመገብ ማምጣት ያለባችሁ መታወቂያችሁን ነው" ብሏል።
በዚህ ሁኔታ ትንሽ ብስጭት የገባቸው ባለስልጣናቱ ይሄ ወከባ የመንግሥት ጊዜ እያቃጠለ ነው ብለዋል።
አኪንዶ ሱሺሮ የተባለው ሬስቶራንት ራሳቸውን ጨምሮ አምስት ጓደኞቻቸው በነፃ እንደሚመገቡ ያሳወቀው በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ በርካቶች 3 ዶላር በመክፈል ስማቸውን የቀየሩ ሲሆን በዚያውም አዲስ መታወቂያ እንዲሁ የምዝገባ ወረቀት እንደሚያገኙ ታይፔይ ታይምስ ዘግቧል።
ጋዜጣው ታይቹንግ ውስጥ የምትገኝ ስሟን የቀየረች ተማሪ ያናገረ ሲሆን በነፃ ሱሺዋን ከተመገበች በኋላ ወደቀደመ ስሟ እንደምትመልሰው ተናግራለች።
በርካቶች መሃል ላይ ሳልመን የሚለውን እየጨመሩ፤ የሳልመን ልዑል፣ የሳልመን ንጉስ፣ የሳልመን የተጠበሰ ሩዝ የሚል ስም መቀየራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ጥሬ አሳና፣ የተቀቀለ ሩዝ ከሌሎች ቅመሞች ጋር የያዘውን ሱሺን ለመብላት በርካቶች ስማቸውን መቀየራቸው ብዙ ቅር እንዳላሰኛቸው ነው።
ሁለት ግለሰቦች እንደተናገሩት 460 ዶላር የሚገመት ሱሺ መብላታቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ገፆቸቻው አስፍረዋል፤ አንደኛውም " ከዚህ በኋላ ሳልመን ለተወሰነ ጊዜ አልበላም" ብሏል።
ምክትል የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቼን ሱንግ የን በበኩላቸው ስም ቅያሬው የመንግሥትን ጊዜ የሚያባክንና አላስፈላጊ ስራዎችንም ያመጣ ነው ብለዋል።
"በርካቶች ያመዛዝናሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁኝ" ብለዋል
ባለስልጣናቱ በአሁኑ ወቅት ዜጎች በህጉ መሰረት ስማቸውን መቀየር የሚችሉት ሶስት ጊዜ እንደሆነም እያስታወሱ ነው።












