ኢራን ‘ድንገተኛ’ የኒውክሌር ፍተሻዎችን አስቆመች

የቃሲም ሱሌይማኒ ግድያ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የነበረውን ውጥረት አባብሶታል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቃሲም ሱሌይማኒ ግድያ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የነበረውን ውጥረት አባብሶታል

ኢራን የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች የኒውክሌር ጣቢያዎችን እንዲመለከት የምትሰጠውን ፈቃድ ለሦስት ወራት ለማራዘም መስማማቷን የድርጅቱ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ኃላፊ አስታወቁ።

ይህ ስምምነት የተባበሩት መንግሥታት ኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ቡድን ከዚህ ቀደም ከነበረው ያነሰ ፈቃድ ከመስጠቱም በላይ ቡድኑ 'ድንገተኛ' ፍተሻዎችን እንዳያደርግ የሚከለክል ነው።

ዶናልድ ትራምፕ በጎርጎሮሳዊያኑ 2015 ከኒውክሌር ስምምነትን መውጣታቸውን ተከትሎ የተጣሉትን ማዕቀቦች ባለማነሳቷ ኢራን የምርመራ ፈቃድ ፖሊሲዋን እየቀየረች ነው።

ዋሽንግተን እና ቴህራን ከስምምነት ለመድረስ የተሻለ ጊዜ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

የትራምፕ አስተዳደር በኢራን ላይ እንደገና ማዕቀቦችን ጥሎ የነበረ ሲሆን ቴህራን በአጸፋው በ2015 ከስድስት ኃያላን ሃገራት ጋር የደረሰችውን ስምምነት ወደ ጎን በመተው የኒውክሌር ማበልጸግን በማስቀጠል ምላሽ ሰጥታለች።

አሜሪካ የ2015ቱን ስምምነትን ሙሉ በሙሉ እስካላከበረች ድረስ እርምጃዎቹን እንደማትቀይር ኢራን አስታውቃለች። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ግን ኢራን መጀመሪያ ለስምምነቱ ተገዢ መሆን አለባት ብለዋል፡፡

በኢራን የኒውክሌር መርሃግብር ቀውስ ለ20 ዓመታት ያህል በዓለም አቀፍ ደረጃ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል። ኢራን የአውቶሚክ መርሃ-ግብሯ ለሠላማዊ ዓላማ የሚውል ነው ስትል፤ አሜሪካ እና ሌሎች አገራት ግን ኢራን በሚስጥር የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ማበልጸግ ትፈልጋለች ይላሉ።

የኢራን እርምጃዎች ምን ማለት ናቸው?

ማክሰኞ በኢራን የፓርላማ አባላት በሥራ ላይ የዋለው ሕግ በዓለም አቀፍ የኒውክሌር ተቆጣጠሪ ቡድን በተገለፁት ወይም ባልታወቁ ጣቢያዎች ድንገተኛ ምርመራ ማድረግ እንዲቆም ይጠይቃል።

ኢራን በ2006 ያስቆመችውን አሰራር በመተው በ2015ቱ ስምምነት መሠረት በኒውክሌር ማብለያ ጣቢያዎቿ ላይ ድንገተኛ እንዲደረግ ተስማምታ ነበር።

ባለፈው ዓመት ድርጅቱ ለመጎብኘት የጠየቃቸውን ሁለት ጣቢያዎችን እንዳይጎበኝ በመደረጉ ለወራት የዘለቀ ውዝግብ ቢከሰትም በኋላ ኢራን ሃሳቧን ቀይራለች።

ባለሙያዎች በ2015ቱ ስምምነት መሠረት በኒውክሌር ጣቢያዎች መደበኛ የሆኑ ምርመራዎች ይቀጥላሉ። አዲሱ ሕግ ተቆጣጣሪዎቹን ማባረር ባያስከትልም ግን ሌሎች ስምምነቶች አለመተግበራቸው ውጥረቱን ከፍ ያደርገዋል።

ኢራን አሁን ለምን ይህን እርምጃ ወሰደች?

ኢራን ከዚህ ውሳኔ የደረሰችው በአሜሪካ እና አገሮቿ በነዳጅ፣ በባንክ እና በፋይናንስ ዘርፍ ላይ የተጣለባትን ማዕቀብ ማስነሳት የአጭር ጊዜ አቅድ በማድረግ ነው።

የኢራን ሕግ የወጣው ጆ ባይደን በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ካሸነፉ በኋላ ነው። ኢራን አዲሱ መሪ ከትራምፕ የበለጠ ለመነጋገር ፈቃደኛ ይሆናሉ የሚል ዕምነት አላት።

የባይደን አስተዳደር ግን አሜሪካ ስምምነቱን እንደገና ከመቀላቀሏ እና ማዕቀቡን ከማንሳቷ በፊት ኢራን የ2015ቱን ስምምነትን ሙሉ በሙሉ እንድታከበር እንደሚፈልግ በግልፅ አሳይቷል።