የትግራይ ቀውስ፡ በትግራይ ክልል እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ተነገረ

የቀይ መስቀል ሰራተኞች እርዳታ ሲያከፋፍሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከፍተኛ ጉዳት ባስከተለው የትግራይ ክልል ግጭት ምክንያት እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር "እጅግ ከፍተኛ " መሆኑን የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አሳሰበ።

የኮሚቴው የኦፕሬሽን ዳይሬክተር ዶሚኒክ ስቲልሃርት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ለቢቢሲ እንደገለጹት "የትግራይ ክልል ሰዎች. . . ሰብል መሰብሰቢያ ወቅታቸውን አጥተዋል" ብለዋል።

ጨምረውም "የሕክምና እርዳታ አቅርቦትን በተለመከተ ከበድ ያሉ ጉዳዮች አሉ" ብለዋል ዳይሬክተሩ።

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ ማቅረቡንና በዚህም 1.5 ሚሊዮን ሰዎች ድጋፍ ማግኘት እንደቻሉ አሳውቆ ነበር።

በግጭቱ ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ የተዘገበ ሲሆን፤ እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለዋል።

በትግራይ ክልል ባሉ የተባበሩት መንግሥታት መጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩ ኤርትራዊያን ስደተኞች በግጭቱ መሃል ተይዘዋል።

ግጭቱ የተከሰተው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ በክልሉ በሚገኘውን የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ካደረሰ በኋላ ነው።

ክልሉን ሲያስተዳድር የነበረው ፓርቲ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ጋር ቁርሾ ከገባ ሰንበትበት ብሎ ነበር።

ጦርነቱን ማሸነፉን ያወጀው ማዕከላዊው መንግሥት ወደ ክልሉ የእርዳታ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙሃን እንዲገቡ አልፈቀደም ተብሎ ይተቻል።

የግጭቱ መንስዔ ምንድነው?

ህወሓት የትግራይ ክልል ለ30 ዓመታት ያክል ያስተዳደረ ፓርቲ ሲሆን በግምት 250 ሺህ ተዋጊዎች እንዳሉት ይነገራል።

ፓርቲው ከሥልጣን የተወገደው የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች ኅዳር 19/2013 የክልሉን ዋና ከተማ መቀለ ከተቆጣጠሩ በኋላ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ሕወሓት የኢትዮጵያን አንድነት ተፈታትኗል፤ እንዲሁም ወታደራዊ ዕዞችን በመያዝ ማዕከላዊውን መንግሥት ለመጣል ጥሯል ሲሉ ይከሳሉ።

ህወሓት በበኩሉ የሰሜን ዕዝን የያዘው ከፌዴራል መንግሥት የሚመጣ ጣልቃ ገብነት ለመከላከል በማሰብ እንደሆነ ይናገራል።

ህወሓት ባለፈው ነሐሴ በክልል ምርጫ አዘጋጅቶ እንደነበር አይዘነጋም። ይህ ደግሞ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ምርጫው በሁሉም አካባቢዎች እንዲራዘም ካደረገው የፌዴራል መንግሥት እርምጃ በተቃራኒ ነው።

የፌደራሉ መንግሥት ምርጫውን ሕጋዊ አይደለም ሲሉ መኮነኑ ይታወሳል።

ነገር ግን ሕወሓት በአፀፋው ማዕከላዊው መንግሥት "ሕጋዊ አይደለም"፤ ኢትዮጵያን የማስተዳደር ሥልጣን የለውም ሲል ቆይቷል።

በዚህ ምክንያት ከጊዜ ጊዜ የተባባሰው ውጥረት ወደ ግጭት አምርቷል።