ሱዳን በኢትዮጵያ ለቀረበባት ክስና ወቀሳ ምላሽ ሰጠች

ሱዳን ባለፈው ሐሙስ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ የቀረበባትን ክስና ወቀሳ በመቃወም ምላሽ ሰጠች።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ ከኢትዮጵያ በኩል የተሰነዘረውን ክስ አጥብቆ የተቸ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ በኩል የወጣውን መግለጫ "በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለውን ግንኙነትና የሁለቱን አገር ሕዝቦች ትስስር የካደ ነው" ማለቱን የአገሪቱ ዜና ወኪል ሱና ዘግቧል።
በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ሁለቱ አገራት በሚዋሰኑበት ድንበር አካባቢ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ሰፍረው ይገኙባቸው የነበሩ ለም የእርሻ ቦታዎችን የግዛቴ አካል ናቸው በማለት ሱዳን ከተቆጣጠረች በኋላ ውዝግብ ላይ መቆየታቸው ይታወሳል።
ወራት ያስቆጠረው የሁለቱ አገራት የድንበር ውዝግብ ከተከሰተ በኋላ የኢትዮጵያ የውጭጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው ጠንካራ መግለጫ በድንበር ይገባኛል ሰበብ "ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት እንዲገቡ የሱዳን የመከላከያ ኃይል በጠብ አጫሪነት የሦስተኛ ወገን መጠቀሚያ ሆኗል" ሲል ከሶ ነበር።
ይህ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የወጣው መግለጫ ከዚህ ቀደም የድንበር ጉዳዩን በተመለከተ ከተሰጡ መግለጫዎች መካከል ጠንካራ መሆኑ የተነገረ ሲሆን "ሱዳንን ዝቅ የሚያደርግና ይቅር የማይባል ስድብ ነው" ስትል ሱዳን ተቃውሞዋን ገልፃለች።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በምላሹ ባወጣው መግለጫ ላይ በሁለቱ አገራት መካከል ስላለው ታሪካዊ ትስስር በመጥቀስ፤ ይህንን ግንኙነት በማስቀጠል ለሕዝቦቹ ደኅንንት፣ መረጋጋትና ምጣኔ ሐብታዊ ልማት እንዲውል ለመስቻል ከፍ ያለ ፍላጎት ሱዳን እንዳላት አመልክቷል።
በሁለቱ አገራት መካከል የተከሰተውን የድንበር ውዝግብ መካረርን ለማርገብና ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ይሁንታን ያገኘ የአፍሪካ ሕብረት ልዑካን ካርቱም ውስጥ መሆናቸውን መግለጫው ጨምሮ ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት "የካደ ነው" በማለት "ሱዳን ላይ ይቅር የማይባል ስድብ" ሰንዝሯል ሲል አጽንኦት ሰጥቷል።
የሱዳን መግለጫ ጨምሮም አወዛጋቢው የድንበር አካባቢ የሱዳን ሉዓላዊ ግዛት መሆኑን አጠንክሮ በመግለጽ፤ ኢትዮጵያ ጉዳዩን ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ወደ ሆኑ ሕጋዊ አማራጮችን ልትወስደው ትችላለች ብሏል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ሐሙስ ባወጣችው መግለጫ የትኛውም ግጭት የሁለቱን አገራት ደኅንነት የሚጎዳና ከባድ ጉዳትን የሚያስከትል መሆኑን እንደምትገነዘብ ጠቁሞ፤ በሱዳን መንግሥት ወታደራዊ ክንፍ እየተበረታታ ያለው ግጭት "በሱዳን ሕዝብ ኪሳራ የሦስተኛ ወገንን ፍላጎት የሚያስፈጽም ነው" ብሎ ከሶ ነበር።
ጨምሮም የድንበር ጥያቄው ሊስተናገድባቸው የሚችሉ በቂ መንገዶች ቢኖሩም "የሱዳን ሠራዊት ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጣስ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽሟል" ብሏል።
እንዲሁም በሁለቱ አገራት መካከል ካለው የትብብርና የወዳጅነት መንፈስ በተቃራኒ "የሱዳን ሠራዊት ንብረቶችን ዘርፏል፣ ካምፖችን አቃጥሏል፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በማጥቃት እንዲፈናቀሉ ያደረገ ሲሆን ባዷቸውን የነበሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት ካምፖችን ተቆጣጥሯል" ሲል ከሷል።
ሱዳንም በበኩሏ በየካቲት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ማብቂያ ላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ግዛቴ ዘልቆ በመግባት ወረራ አካሂዷል በማለት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል መክሷ ይታወሳል።
የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በድንበር ውዝግቡ ምክንያት ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ የገለጹ ሲሆን በድንበር አካካቢ ያለው ሁኔታ ግን በውጥረት ውስጥ መሆኑን ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት ሱዳን በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሯን ለምክክር በሚል ወደ ካርቱም የጠራች ሲሆን ይህም ከድንበር ውዝግቡ ጋር የተገናኛ ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።
ሱዳን ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ለረጅም ጊዜ ይገባኛል ስትላቸው የነበሩትን በርካታ የድንበር አካባቢዎችን ሠራዊቷን በማሰማራት የተቆጣጠረች ሲሆን፤ ባለስልጣናቷም በቁጥጥራቸው ስር ያስገቡት ሕጋዊ ግዛታቸው መሆኑን በመግለጽ ይዞታቸውን ሲያጠናክሩ ቆይተዋል።
የሱዳንን እርምጃ ተከትሎ ኢትዮጵያ የድንበር አካባቢው ይዞታ ወደነበረበት እንዲመለስና ሁለቱ አገራት ችግሩን ቀደም ሲል ጀምረውት በነበረው የድንበር ኮሚሽን በኩል በውይይት እንዲፈቱት በተደጋጋሚ መጠየቋ ይታወሳል።














