የፈረንሳይ ቱሪስትን የቀላው አልጄሪያዊ ሞት ተፈረደበት

የ55 ዓመቱ ሐርቪ ጎርደል ጁርጁራ አስከሬን

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአልጄሪያ ፍርድ ቤት በ2014 አንድ የፈረንሳይ ቱሪስትን በጭካኔ ቀልቷል ያለውን ዜጋ በሞት እንዲቀጣ ወሰነ።

የ55 ዓመቱ ሐርቪ ጎርደል ጁርጁራ በሚባለው የአልጄሪያ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በጉብኝት ላይ ሳለ ነበር ተጠልፎ የታገተውና በኋላም የተገደለው።

ክስተቱ በወቅቱ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል።

ቱሪስቱ በግፍ የተቀላበትን ዝርዝር የሚያሳይ የቪዲዮ ምሥል ጁንድ አል ካሊፋ በሚባል ጽንፈኛ ቡድን በኩል ተለቅቆ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ዓለም አቀፍ ውግዘትን ያስከተለ ነበር።

ጁንድ አል ካሊፋ ለድርጊቱ ኃላፊነቱን የወሰደና የአይ ኤስ ደጋፊ የሆነ ጽንፈኛ ቡድን ነው።

የዚህ ቡድን አባል እንደሆነ የተጠረጠረው አብዱልማሊክ ሐምዛይ ትናንት ሐሙስ ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር። የእርሱ ባልደረቦችም በሌሉበት ጉዳያቸው እየታየ ይገኛል።

ምንም እንኳ ይህ አልጄሪያዊ በግድያው እንዳልተሳተፈ ቢናገርም ፍርድ ቤት ተቀባይነት አላገኘም።

"በኔ ላይ ሞት እየፈረዳችሁ ያላችሁት ይህን ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመዝጋትና ፈረንሳዮችን ለማስደሰት ነው፤ እኔ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ብሏል" ፍርደኛው አብዱልማሊክ።

ሆኖም ሟች ጋ አብረው ተራራ ይወጡ የነበሩ ሰዎች አብዱልመሊክ ከአጋቾቻቸው አንዱ እንደነበረ መስክረውበታል።

ሟች ሚስተር ጎርደል ልምድ ያለው ተራራ ወጪ ቱሪስት ሲሆን በመስከረም 2014 ይህንኑ በማድረግ ላይ እያለ ነበር በጽንፈኛ ቡድኑ የታገተው።

አጋቾቹ ፈረንሳይ በኢራቅና በሶሪያ ኢዝላሚክ ስቴት ላይ የምታደርገውን የአየር ጥቃት ካላቆመች ዜጋዋን እንደሚቀሉ አስጠንቅቀው የነበረ ሲሆን ፈረንሳይ ግን የአጋቾቹን ጥያቄ አልተቀበለችም።

በዚያ ወቅት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት የነበሩት ፍራንኮይስ ሆላንዴ ድርጊቱን ጨካኝና የፈሪ ተግባር ሲሉ ኮንነውት ነበር።

የሟቹ ፈረንሳዊ አስክሬን እስከ ጥር 2015 አልተገኘም ነበር። አልጄሪያ በሺ የሚቆጠሩ አስክሬን አፈላላጊዎችን ካሰማራች በኋላ ነበር በብዙ ፍለጋ የተገኘው።