የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ የቀድሞ ባለቤት 4 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ሰጠች

ማኬንዚ ስኮት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማኬንዚ ስኮት ለምግብና አስቸኳይ ጊዜ የሚሆን 4 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ሰጠች። ገንዘቡ ከአንድ ግለሰብ በአራት ወራት ውስጥ ብቻ የተሰጠ ከፍተኛ እርዳታ ሆኖ ተመዝግቧል።

ማኬንዚ ስኮት በጦማሯ ላይ እንዳለችው ገንዘቡ በወረርሽኙ ምክንያት ኑሮ ዳገት የሆነባቸው አሜሪካዊያንን የሚያግዝ ነው።

ማኬንዚ ስኮት በዓለም 18ኛዋ ሀብታም ናት።

በቅርቡም የሀብት መጠኗ በዚህ ዓመት ብቻ በ23 ቢሊዮን ዶላር ጨምሮ አሁን በድምሩ ወደ 60 ቢሊየን ዶላር ተመንድጎላታል።

አብዛኛው የሀብቷ ምንጭ ታዲያ ከቀድሞ ባለቤቷ ፍቺ በኋላ በፍርድ ቤት የተወሰነላት ገንዘብ ነው። ግለሰቧ የዓለም ቁጥር አንድ ሀብታም የአማዞኑ ጌታ ጄፍ ቤዞስ የቀድሞ ባለቤቱ መሆኗ ይታወቃል።

"ይህ ወረርሽኝ የብዙ አሜሪካዊያንን ሕይወት አመሳቅሏል" ያለለችው ስኮት ከ6500 የእርዳታ ድርጅቶች ውስጥ 380 የሚሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ነቅሳ በማውጣት ገንዘቡን እንደሰጠች ገልጻለች።

"የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዙ በተለይ በሴቶችና በጥቁር አሜሪካውያን ላይ ፈተናን ደቅኗል። ቢሊዮኖች ግን ሀብታቸው ይበልጥ እያበጠ ነው" ያለችው ስኮት ባለፈው ሐምሌም በተመሳሳይ ወደ 2 ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ መለገሷ የሚታወስ ነው።

ስኮት በዚህ ዓመት ብቻ በድምሩ 6 ቢሊዮን ዶላር በመስጠት ለጋስነቷን አስመስክራለች።

ባለፈው ዓመት ደግሞ አብዛኛውን ሀብቷን ለበጎ አድራጎት ለማዋል "ጊቪንግ ፕሌጅ" የተሰኘውን የቃልኪዳን ሰነድ ፈርማለች።

"ጊቪንግ ፕሌጅ" የዓለም ቢሊዮነሮችና ቤተሰቦቻቸው ሀብታቸውን ለበጎ አድራጎት ለማዋል መስማማታቸውን የሚገልጡበት ሰነድ ነው።

ስኮት ይህን ልግስናዋን ተከትሎ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አድናቆታቸውን እየገለጡላት ነው። የገንዘቡ ትልቅ መሆን ብቻም ሳይሆን ስኮት ጊዜ ወስዳ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን መርጣ በተጠና ሁኔታ ገንዘቡን መለገሷን ወደውላታል።

በዚህ ዓመት የቀድሞ ባሏ ጄፍ ቤዞስም ለአየር ንብረት ለውጥ ጥናትና ምርምር 10 ቢሊዮን ዶላር መለገሱን ይፋ አድርጎ ነበር።

ባለፈው ህዳር ወር የዚህን ገንዘብ የመጀመርያ ዙር እርዳታ ለ16 ድርጅቶች አከፋፍሏል። 10 ቢሊዮኑ በብዙ ዓመታት የሚቸር የገንዘብ መጠን ሲሆን ባለፈው ወር 800 ሚሊየኑ ወጪ ተደርጓል።

ቤዞስ የሀብት መጠኑ በዚህ ዓመት ብቻ በ70 ቢሊዮን ዶላር ጨምሮ አሁን በጥቅላላው 185 ቢሊዮን ዘሏል።

ብሉምበርግ እንደሚለው ጄፍ ቤዞስን የመሰለ ሀብታም በምድር ላይ የለም።

ይህ ከፍተኛ የሀብት ጭማሪ ወረርሽኙ ያመጣለት አዱኛ እንደሆነ ተዘግቧል። ይህም ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት ቤት በመቀመጣቸው የኦንላይን ግብይቱ እየደራ መምጣቱ ነው።