የፓኪስታን ፕሬዝዳንት ደፋሪዎች ላይ ከባድ ቅጣት የሚጥል ሕግ ላይ ፈረሙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፓኪስታን ፕሬዝዳንት በመድፈር ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች በፍጥነት የቅጣት ውሳኔ እንዲተላለፍባቸው እንዲሁም ጠንከር ያለ ቅጣት እንዲጣልባቸው የሚያስችል ሕግ ላይ ፊርማቸውን አኖሩ።
ይህ ሕግ በአገር አቀፍ ደረጃ የብሔራዊ የፆታ ጥቃት አድራሾች ምዝገባ ሥርዓት ማካሄድን፣ ጥቃት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ማንነት መደበቅንና የተወሰኑ ጥቃት አድራሾችን በኬሚካል ማኮላሸትን ይፈቅዳል።
የመድፈር ወንጀሎችን በፍጥነት የሚቋቋሙ ችሎቶች ጉዳዩን እንዲመለከቱ የሚደረግ ሲሆን በአራት ወር ውስጥም ውሳኔ ሰጥተው ፋይሉን ይዘጋሉ ተብሏል።
ይህ የፕሬዝዳንቱ ያፀደቁት ሕግ የተሰማው ከላሆሬ ከተማ ወጣ ባለ ስፍራ በቡድን የተደፈረች ሴት ታሪክ የሕዝብ ቁጣና ተቃውሞ ከቀሰቀሰ በኋላ ነው።
ጥቃት የደረሰባት ሴት የተደፈረችው ወደ ከተማዋ በሚያመራ አውራ ጎዳና አጠገብ ሲሆን ሁለት ልጆቿም ጥቃቱ እናታቸው ላይ ሲፈፀም በስፍራው ነበሩ ተብሏል።
በወቅቱ የላሆሬ ፖሊስ ከፍተኛ ባለስልጣን ጥቃት የደረሰባት ሴት ለወንጀሉ በከፊል አስተዋጽኦ አድርጋለች ሲሉ መናገራቸው ተሰምቷል።
የኃላፊው አስተያየት እና ድርጊት ፓኪስታናውያንንን በቁጣ ወደ አደባባይ እንዲወጡ ያደረገ ሲሆን መንግሥትም አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ ቃል እንዲገባ አስገድዶታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካኻን እና ካቢኔያቸው ሕጋዊ እርምጃውን ያፀደቁት ባለፈው ወር ሲሆን ፕሬዝዳንት አሪፍ አልቪ በበኩላቸው ሕጉ ላይ ፊርማቸውን ያዋሉት ዛሬ ማክሰኞ እለት ነው።
መንግሥት በ120 ቀናት ውስጥ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ሕግ ሆኖ እንዲፀድቅ ማድረግ የሚጠበቅበት ይሆናል።
አንዳንዶች ፕሬዝዳንቱ ፊርማቸውን ያኖሩበትን ሕግ ከባድ ቅጣት ይዟል በሚል ትችታቸውን እያሰሙ ነው። አክለውም ባለስልጣናቱ ሕጉን ከማጽደቃቸው በፊት አስፈላጊውን ምክክር አላካሄዱም ብለዋል።
ኢንዶኔዢያ እንዲሁም ፖላንድ ሕጻናትን የሚደፍሩ ሰዎች በኬሚካል እንዲኮላሹ የሚያስገድድ ሕግ ያጸደቁት እኤአ በ2016 እና በ2009 ነው።
በፓኪስታን ጾታዊ ጥቃት የሚያጋጥማቸው ሴቶች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መሆኑ ይነገራል።
በ2015 እኤአ አንዲት ሴት በቡድን ስትደፈር የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ የተሰራጨ ሲሆን ፓኪስታን ይህ እንዳይሆን መከልከል የሚያስችል ሕግ የላትም።
















